
ኢትዮጵያን ለአሁኑም ይሁን ለቀጣዩ ትውልድ የተመቸች ሀገር ማድረግ የሚያስችሉ የልማትና ግንባታ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን መመልከታቸውን ወደ ሀገር ቤት የገቡ ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ተናገሩ።
በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚኖሩ ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ከታህሳስ 20 ቀን 2016 እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም በሶስት ዙር ወደ ሀገር ቤት እንዲመጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
የመጀመሪያው ዙር ከታህሳስ 20 እስከ ጥር 20/2016 ድረስ የሚቆይ ሆኖ ‘connect to your culture’ በሚል የተደረገ ጥሪ ሲሆን፤ ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ የዳያስፖራ አባላት የገና በዓልን ማክበራቸውንና ሌሎች በዓላት ላይ እንደሚታደሙ ተናግረዋል።
በዚህም መሰረት በመጀመሪያው ዙር ወደ ሀገር ቤት የመጡ ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ጉብኝት አድርገዋል።
በጉብኝታቸውም በተመለከቷቸው ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችና የቱሪስት መስህቦች በእጅጉ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ኢዜአ ካነጋገራቸው ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን መካከል ከ10 ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ልዑል ፍትሃነገስት በኢትዮጵያ ለትውልድ የሚጠቅሙ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን መመልከቱን ተናግሯል።
በኢትዮጵያዊነቱ ሁሌም ክብርና ኩራት እንደሚሰማው የተናገረው ልዑል ወደ ሀገሩ መጥቶ በተመለከተው ነገር ሁሉ መደነቁንና መደሰቱን ጭምር ገልጿል።
በየአመቱ ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ አዳዲስ ለውጦችን እንደምታስተውል የተናገረችው ደግሞ ከለንደን የመጣችው ነኢማ ሰሚር ነች።
በርካታ አዳዲስ የሚያስደንቁ ፕሮጅክቶች ተሰርተዋል የምትለው ነኢማ እነዚህን ፕሮጀክቶች በአካል ተገኝቼ በመጎብኘቴ በሚዲያ የሰማሁትን በአካል እንዳረጋግጥ አስችሎኛል ስትል ተናግራለች።
ኢትዮጵያን ለአሁኑም ይሁን ለቀጣዩ ትውልድ የተመቸች ሀገር ማድረግ የሚያስችሉ አስደናቂ የልማትና ግንባታ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን መመልከታቸውን ገልጸዋል።
በመጀመሪያው ዙር ከታህሳስ 20 እስከ ጥር 20/2016 ድረስ ጥሪውን ተከትለው ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ደግሞ ‘connect to your history’ በሚል በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ወቅት እንዲመጡ ጥሪ ቀርቧል።
ሶስተኛው ዙር ‘leave your legacy’ በሚል በኢትዮጵያ ከክረምት ወቅት ጀምሮ እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
