የባንኩን ገንዘብ ተመላሽ ያላደረጉ ግለሰቦች መረጃ ላይ ክትትል በማድረግ ተጠያቂነትን ለማስፈን ይሰራል ፦ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት::

Spread the love

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሲስተም ብልሽት ባጋጠመው ወቅት ጤናማ ያልሆነ የገንዘብ እንቅስቃሴ ያደረጉ እና በእስካሁኑ ገንዘቡን ተመላሽ ያላደረጉ ግለሰቦች መረጃ ላይ ክትትል በማድረግ ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚሰራ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ገለፀ፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጅታል የባንክ ሥርዓት በጊዜያዊነት መቋረጥን አስመልክቶ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ባወጣው መግለጫ፤ በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ መጠቀም የህግ ተጠያቂነት እንደሚያስከትል ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲጂታል ባንክንግ ስርዓት ላይ መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም ያጋጠመውን ችግር ተከትሎ ጤናማ ያልሆኑ የገንዘብ እንቅስቃሴዎች የተደረጉ መሆናቸውን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ተገንዝቦ አስፈላጊውን ሥራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝም አስታውቋል።

ችግሩ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ አገልግሎቱ መስሪያ ቤቱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቅሷል፡፡

በተለይም የራሳቸው ያልሆነን ገንዘብ ያንቀሳቀሱ እና ወጪ ያደረጉ ግለሰቦች ገንዘቡን ተመላሽ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ በርካቶች አለአግባብ የወሰዱትን ገንዘብ ተመላሽ እያደረጉ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊና የራስ አስመስሎ የማቅረብና የመጠቀም ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ኃላፊነት ከተሰጣቸው ተቋማት መካከል አንዱ ሲሆን ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 መሰረት በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ/ንብረት መወረስ እንደተጠበቀ ሆኖ እንደ ወንጀሉ ክብደት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ሆኖ መደንገጉን ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ልዩ ልዩ ወንጀሎችን በመፈጸም የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና መጠቀም በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ አገልግሎቱ በራሱ እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የሚያከናውናቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጠል ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲጂታል ባንኪንግ ችግር ማጋጠም ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ክፍተት ጤናማ ያልሆነ የገንዘብ እንቅስቃሴ ያደረጉና በእስካሁኑ ገንዘቡን ተመላሽ ያላደረጉ ግለሰቦች መረጃ ላይ አገልግሎቱ ክትትል በማድረግ ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚሰራም አረጋግጧል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *