
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አምስት ተጨማሪ የሀገር ውስጥ መዳረሻ ኤርፖርቶችን እየገነባ መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን ለማስፋት እየሰራ ነው።
የሚያበራቸውን አውሮፕላኖች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ አየር መንገዱ 136 ዓለም አቀፍ እንዲሁም 22 የሀገር ውስጥ መዳረሻዎች እንዳሉት ገልጸዋል።
አየር መንገዱ ተጨማሪ የሀገር ውስጥ መዳረሻዎችን ለማስፋት የያዘውን ዕቅድ ተከትሎ በአሁኑ ወቅት አምስት የሀገር ውስጥ መዳረሻ ኤርፖርቶችን እየገነባ መሆኑን ተናግረዋል።
ኤርፖርቶቹ የሚገነቡት ሚዛን አማን፣ ነጌሌ ቦረና፣ ያቤሎ፣ ጎሬ መቱና ደብረ ማርቆስ መሆናቸውን ገልጸው፤ አራቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ወደ ሥራ እንደሚገቡ ጠቁመዋል።
ይህም በሀገር ውስጥ ያሉ ደንበኞች ፍላጎትን ተከትሎ የሚተገበር ሲሆን፤ በቀጣይም ሌሎች መዳረሻዎች ጥናት ላይ በተመሠረተ መልኩ ግንባታ የሚቀጥል ይሆናል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል ጉዳት የደረሰባቸው የአክሱምና የቀብሪደሃር ኤርፖርቶች እድሳት እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገቡም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
አየር መንገዱ በቀጣይም የሀገር ውስጥ መዳረሻዎችን ለማስፋት በትኩረት እንደሚሰራም ዋና ስራ አስፈጻሚው ጨምረው ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2035 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 25 ቢሊየን ዶላር ከፍ ለማድረግና በዓመት 67 ሚሊየን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል።
ኢዜአ
