ከተሞች ያላቸው መሠረታዊ ሀብት መሬት ነው።

Spread the love

ውስንና ውድ የሆነውን የከተማ መሬት በአግባቡ መለየት፣በፕላን መምራትና ማስመዝገብ ካልተቻለ ከተሞች ሀብት የማመንጨት ውስንነት፣አስፈላጊ መሠረተ ልማቶችን ያለማሟላት፣ የመልማት ችግርና ለህገወጥነትና ለተለያዩ ብልሹ አስራሮች ተጋላጭ ይሆናሉ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ክልሉ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ የከተማ መሬት አስተዳደር ጋር በተያያዘ የይዞታና ምዝገባ፣ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን ማዘመንና የመሬት አቅርቦትና ስርጭትን ከማሳለጥ አኳያ ሰፊ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል። ከእነዚህም ውስጥ የካዳስተር ስራ በዋናነት ይጠቀሳል።

የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር የማታለም ቸኮል በክልሉ በሁለት ዓመት ውስጥ በካዳስተር 6ሺህ 4መቶ ህጋዊ ሠርተፍኬት ያላቸው የከተማ መሬቶች መመዝገባቸውን ገልፀው የከተማ መሬቶችን በተገቢው በመለየት፣በፕላን በመምራትና በመመዝገብ ከህገወጥና ከብልሹ አሠራሮች ለመከላከል በቅንጅትና በትብብር መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በክልሉ በህጋዊ መንገድ መሬት ተለክቶ ተገቢ ሠርተፍኬት ያላቸው፣ በተወሰነ አስለክተው ሠርተፍኬት በመያዝ መሬቱን በማስፋፋት ግብር የማይከፍሉ፣ የመንግሥት እና የግለሰብ የጋራ ሀብት የነበሩ የግጦሽ መሬትና ያለህጋዊ ሰነድ የተወረሩ እና በከተማ ውስጥ ያሉ የአርሶ አደር መሬቶችን በመለየት ስርዓት ለማስያዝ በክልል ደረጃ በመሬት አስተዳደር ዙሪያ በሶስት ዓመት ተግባራዊ የሚሆን አዋጅ ወጥተው እየተተገበረ እንደሚገኝ ኢንጂነር የማታለም ቸኮል ተናግረዋል።

ሳይፈቀድ የተያዙ መሬቶችን የከተማ ፕላንና ሊዝ ህግን በማይጣረስ መልኩ በፕላኑ መሠረት የተሰሩትን በሊዝ ህጋዊ የማድረግና የፕላን ጥሰት ያለባቸውን ከቦታው በማስነሳት ተለዋጭ መሬቶችን በማዘጋጀት ግለሰቦች ችግር ውስጥ እንዳይገቡ የማድረግ ስራ እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው በዚህም ሠርተፍኬት የሌላቸው ከ32 ሺ በላይ ግለሰቦች በማዘጋጃ ቤቶች እንዲመዘገቡ በማድረግ እልባት ለመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በክልሉ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ከመሬት አቅርቦትና ዝግጅት አኳያ የተሻሉ ስራዎች ተሠርቷል ያሉት ኢንጂነር የማታለም እስከአሁን በመሬት ዝግጅት በሁለት ዓመት 2ሺ 93 ሄክታር መሬት ለኢንቨስትመንት፣ለማህበራትና ለተለያዩ ጉዳዮች ተዘጋጅተው ከዚህም 1ሺ 341 ሄክታር መሬት ሊተላለፍ መቻሉንም አረጋግጠዋል።

ከከተማ መሬት ፍላጎት አንፃር እንደክልል ገና ብዙ ስራዎችን መስራት እንደሚጠበቅ ያወሱት ኃላፊው እስካሁን 11ሺ 3 መቶ ፓርስል መሬት በካዳስተር ንባብ ተወስደው እንደተረጋገጠ ከዚህ ውስጥ 6ሺ 440 ፓርስል በካዳስተር መመዝገቡ፣ሰነድ ሳይሰጣቸው ለቆዩ 9ሺ 4መቶ 65 ሰዎች የመሬት ይዞታ ሰነድ መሰጠታቸው እንዲሁም  በማስፋፊያ የተያዙ ከገጠር ወደ ከተማ የገቡ አርሶአደሮች 4ሺ 609 ፓርስል መሬት ተለክተው ጊዜያዊ ሠርትፍኬት መስጠት መቻሉም ገልፀዋል።

በክልሉ የሚገኙ የከተማ መሬቶችን በፕላን በመምራት መንግስት ያለውን ሀብት አውቆ ከከተሞች ከሚገኘው ሀብት ለከተሞች አሰፈላጊ መሠረተ ልማቶችን እንዲያሟላና ህዝቡም የሀብቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ከተሞችን በፕላን ለመምራት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ያሉት ኢንጂነር የማታለሞ የከተማ አስተዳደሮች፣ማዘጋጃ ቤቶችና የመንግስት መዋቅሮች ያላቸውን ሀብት በማስመዝገብ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በክልሉ በሚገኙ በዋና ዋና ከተሞች ላይ ቀድሞ የነበሩ ፕላኖችን በማሻሻልና ፕላን ላልተሰራባቸው ደግሞ ፕላን መስራት መቻሉን ነው የገለፁት ኃላፊው።

ከክልሉ ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እና በዘርፉ ከተዋቀረ ኮሚቴ ጋር በመናበብ በተለያዩ ከተሞች በክራይ ሰብሳቢነት ለግለሰቦችና ለማህበራት ያለአግባብ የተተላለፉ መሬቶች ላይ እርምጃ በመውሰድ ለብልሹ አሰራር ተባባሪ የሆኑ ግለሰቦችና የመንግስት አካላት በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ኃላፊው አንስተዋል።

ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ጋር በተያያዘ  ከህብረተሰቡ ለሚነሱ ቅሬታዎች ከእጅ ንክክ ነጻ በሆነ መንገድ አገልግሎት ለመስጠት ከኢፌዲሪ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር የለማ ሶፍትዌርን ቦንጋና ሚዛን ከተሞች እንዲጠቀሙ የማላመድና ኔትወርክ የመዘርጋት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝና በቀጣይ በሁሉም ከተሞች ለማስፋት ትኩረት ይደረጋል ብለዋል ኃላፊው።

በዘላቂነት ስራው ሲጠናከር ከመሬት ልማት፣ ከህንፃ አዋጅና ከቀበሌ ቤቶች ጋር የሚያያዙ አድሎአዊና ብልሹ አሰራሮች ይፈታሉ ያሉት ኃላፊው በየከተሞች ያሉ ፋይሎች  በአግባቡ ካለመያዛቸው የተነሳ ለተለያዩ ብልሹ አሰራሮች ተጋላጭ ስለሚሆኑ መረጃዎችን እስካን በማድረግ ወደ ሶፍት ኮፒ ለመቀየር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሚታየውን የግብዓት እጥረት ቢሮው የአቅሙን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች ሊፈቱ የሚገቡ የማዘጋጃ ቤታዊ አግልግሎት ጉዳዮችን ከንቲባዎች በሳምንት አንዴ እንዲፈቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የከንቲባ ችሎት ተመቋቁመው ወደ ስራ መገባቱን ኢንጂነሩ ገልጸዋል።

በክልሉ ቀጣይ ሳይፈቀድ የተያዘ መሬት በከተማ ፕላን መሰረት ሥርዓት ማስያዝ፣የመሬት መብት ምዝገባ ሥራና ከነዚህ ሥራዎች የሚገኘውን ሀብት ለከተማ መሰረተ ልማት ማዋልና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎታ ማሻሻል በትኩረት የሚሰሩ ሲሆኑ መንግስት፣ባለድርሻ ተቋማት እንዲሁም ህብረተሰቡ ለስራው ስኬታማነት እንዲተባበርና የነቃ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባ ጥሪ አስተላልፏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *