



የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በቴክኖሎጂ የዘመኑ ከተሞችን ለመገንባት እና የዜጎችን የአኗኗር ሁኔታ ለማሻሻል ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ተደራሽነትን ማስፋት፣ ለዜጎች እኩል ዕድል መፍጠር እንዲሁም በዜጎችና ተቋማት መካከል መተማመንን ማጎልበት የስትራቴጂው ቁልፍ ትልሞች መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወቃል።
እነዚህን ትልሞች ለማሳካት የሕዝብ ዲጂታል መሠረተ ልማትን ማስፋፋት ቁልፍ ተግባር መሆኑን ጠቅሰው ይህም ቴክኖሎጂን ሰው ተኮር በማድረግ የዜጎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ ለማሻሻል ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የመደመር መንግሥት ከተሞች የፈጠራ፣ የቴክኖሎጂና የብልጽግና ማሳያ እንዲሆኑ እየሰራ ነው።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ከተሞችን ስሉጥ(ስማርት ሲቲ) ማድረግ የሚያስችል ጠንካራ መሠረት መጣሉን ተናግረዋል፡፡
ይህም ከተሞች ከዕቅድ ዝግጅት ጀምሮ በዲጂታል መንገድ እንዲመሩ በማስቻል እና የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
በዚህም ለነዋሪዎች ምቹ ከተማ፣ የኤሌክትሮኒክ ግብይት እንዲሁም ለዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት የተቻለበት እንደነበረ አንስተዋል።
በዚህም የሚታይ ውጤት እና ለከተሞች እድገት ትልቅ መሰረት ጥሎ በስኬት መጠናቀቁን ገልፀዋል።
አዲሱ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ከተሞች ከስማርት ከተማነት ባለፈ በቴክኖሎጂ የዘመኑ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
አዲሱ የከተማ ልማት ፖሊሲም ከስትራቴጂው ጋር በቀጥታ የሚዛመድ ሲሆን፤ የኃይል አጠቃቀምን፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን፣ የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያሰርጽ መሆኑን አስረድተዋል።
ዲጂታላይዜሽን በዜጎችና በመንግሥት እንዲሁም በአገልግሎት ሰጭና ተቀባይ መካከል መተማመንን የሚፈጥር መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
የመረጃ ደኅንነትን በማረጋገጥ መረጃዎችን ለሀገር ዕድገት የመጠቀም ልምድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መምጣቱንም ለአብነት ጠቅሰዋል።
የመደመር መንግሥት ከተሞች የፈጠራ፣ የቴክኖሎጂ እና የብልጽግና ማሳያ እንዲሆኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንና ዲጂታላይዜሽን ለዚህ ስኬት ዋነኛው የመስፈንጠሪያ አቅም መሆኑንም ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
