




ግልፀኝነት የሰፈነውን ጨረታ ሂደት ለማስፈንና ውጤታማ ግዥ ለማስፈጸም የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት ወሳኝ መሆኑ ተመላከተ
የፈደራል ግዥና ንብረት ባለስልጣል ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያዊ ክልል ማዕከል ለተመረጡ ግዥ ባለሙያዎች የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት ላይ ስልጠና በቦንጋ ከተማ እየሰጠ ነው።
በመክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ የሺሐረግ ደበበ የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት እኩል የውድድር እድል መፍጠር፣ ገንዘብ የሚያስገኘውን ዋጋ ማስገኘት፣ የህዝብ ግዥ ህግን ማስከበር፣ ወጪ መቀነስና ጊዜ መቆጠብ፣ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን ማስፈን፣ ውጤታማነትን ማሻሻል፣ የህዝብና የግል ሴክተሮችን ያካተተ የቀናጀና የተናበበ ስነምህዳር መፍጠር የስርዓቱ ዋና ዋና ጥቅሞች ናቸው ብለዋል።
ግዥ ፈፃሚ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የተመደበላቸውን ውስን ሀብት ለግዥ ሲያዉሉ ውጤታማ እና ለታለመለት ዓላማ እንዲያውሉ እንድሁም ከማነኛውም ንኪኪ የጸዳ እንድሆን የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ወሳኝ መሆኑን አውስተዋል።
እንደ ሀገር በ9 የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ተጀምረው አሁን ላይ 262 የመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ እየተተገበረ ያለው የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት ውጤታማነቱ ተረጋግጦ ክልላችንም ወደ ማስጀመሪያ ምዕራፍ መሻገሩ የክልሉ መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የፌዴራል የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የኤሌክትሮኒክ ግዥ ትግበራን ለማስጀመር ቁሳዊና ስልጠና ድጋፎችን መስጠቱን የገለፁት ወ/ሮ የሺሐረግ ወደስራ ሲገባ ልያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ወደ እድል በመቀየር እንደ ሀገር የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ ከዳር ማድረስ እንደሚቻልም ገልፀዋል።
እንደ ክልል በሁሉም መስክ ውጤቶች እየተመዘገቡ እንዳሉ ያወሱት ዋና ዳይረክተሯ በተወሰነ መልኩ በጨረታ ሂደት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ለቅሬታና አቤቱታ ምንጭ ከመሆኑም ባሻገር ልማቱ በተፈለገበት ጊዜ እንዳይሳለጥ የሚያደናቅፈውን አሰራር ለማስተካከል የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ማስፈለጉን አብራርተዋል።
ለዝሁ ምዕራፍ ስለመድረሳችን የክልሉ መንግስት ለትግራ ባለው ቆራጥ አቋም ከፌዴራል ግዥና ንብረት ባለስልጣን እየሰጠ ላለው ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልፀው በመርሃግብሩ ላይ የተገኙት ሰልጣኞች ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል።
በስልጠናው ላይ ከፌደራል እና ከክልል የተገኙ አመራሮችና ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን በተግባር ላይ ትኩረት ያደረገው ስልጠናው ለሶስት ተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥ ከመርሃ ግብሩ መረዳት ተችሏል።
በአሻግሬ ገ/ወልድ
