ራሱን “ፋኖ” ብሎ የሚጠራው ጽንፈኛ ቡድንና ሸኔ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

Spread the love

ራሱን “ፋኖ” ብሎ የሚጠራው ጽንፈኛ ቡድንና ሸኔ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። የራሴ የሚሉትንም የጣላቴ የሚሉትን በአምላክ አምሳያ የተፈጠረውን ክቡር የሰው ልጅ ህይወትን አውሬ እንኳን በማይፈጽመው መልኩ በአስከፊ ሁኔታ በሁሉም አማራጮች ይገድላሉ። ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ሰላሌ -ደራ አካባቢ ጽንፈኛው ቡድን የፈፀመው የአረመኔነት ተግባር ይህንኑ የሚያመለክት ነው። ይህ ፈጽሞ ከሰው ልጅ የማይጠበቅ አፀያፊ ድርጊት መወገዝ አለበት።

ዓላማቸው ሁለት ነው። አንዱ ዓላማ በዚህ አሰቃቂ ድርጊት አንዱ ብሔር በሌላኛው ላይ ተነሳስቶ እልቂትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ማድረግ ነው። በዚህም እኩይ ፍላጎታቸውን ማሳከት ነው። ሌላኛው ዓላማቸው በዚህ ኢሞራላዊ ድርጊታቸው በህዝብ ዘንድ ፍርሃት በማንገስ ያሻቸውን ማድረግ ነው። ሁለቱም ሞታቸውን ያፋጥነዋል እንጂ የሚሳካ አይደለም። ቅዥት እና እኔ ብቻ የሚል ጫፍ የረገጠ ጽንፈኝነት የሚወልደው በመሆኑ እንዲህ አይነት እኩይ ፍላጎት መቼም ቢሆን ተቀባይነት የለውም ብቻ ሳይሆን አይሳካም።

የአንድን ማህበረሰብ ልብ መግዛት የሚቻለው፣ በዚህም የትኛውንም አይነት ፍላጎት ከግብ ማድረስ የሚቻለው ምክንያታዊ በመሆን እና የማህበረሰቡን ህግጋትና ሞራላዊ እሴቶች በመጠበቅ ነው። ለማመን የሚከብደን ኢሞራላዊ ድርጊት በመፈፀም በዓለማችን የትግል እንቅስቃሴ ውስጥ የቆመለትን ግብ ያሳካ የለም። ለጊዜው አንዳንዶቹ ኢሞራላዊ ድርጊቶች አንድን ውጥን ያሳኩ ይመስሉ ይሆናል። ይህ እንዳልሆነ የፋሽስቶች ታሪክ ምስክር ነው።
በሁለቱም አቅጣጫ ሰሞኑን በሰላሌ ደራ ላይ የተፈፀመው አጅግ ሊወገዝ የሚገባው አይነት ሰውኛ ያልሆኑ ድርጊቶች በመፈጸም አማራና ኦሮሞን ለመጨረስ ያልተሞከረበት ጊዜ የለም። ግን ሁሉም አልተሳኩም ብቻ ሳይሆን በዚህ አይነት ኢሞራላዊ ሁኔታ መቼም ቢሆን አይሳካም። ምክንያቱም የሰው ልጅ በተፈጥሮው ሚዛናዊ፣ ትርፍና ኪሳራን ለይቶ በምክንያታዊነት አቋም የሚወስድና ወደ ድርጊት የሚገባ ነው። ሸኔ እና ጽንፈኛው ጃውሳ በሚፈጽሙት አሠቃቂ ድርጊቶች ሁለቱን የተወለዱ፣ የተገመዱ፣ ከሌሎች ወንድም እህቶቻቸው ጋር በመሆን በከፈሉት መስዋዕትነት ኢትዮጵያን ያፀኑትን ህዝቦች በማጋጨት የትኛውንም አይነት እኩይ ፍላጎት ማሳካት አይቻልም።

የጽንፈኞች ፍላጎት ከማፍረስ እና ብጥብጥ ከመፍጠር የተሻገረ አይደለም። ፍላጎታቸው የህዝብ ጥቅም እና መብት ማስከበር ቢሆን ለምን ንጹሃንን ፣ ምስኪን፣ ራሳቸውን መካለከል የማይችሉ ሰዎችን ለምን ይገድላሉ ፣ ያርዳሉ፣ ይዘርፋሉ፣ ሴቶች ይደፍራሉ፣ የህዝብና ግለሰቦች ሃብትና ንብረት ያወድማሉ? ዓላማቸው የራሳቸውን እና የሌሎች ሃይሎችን ፍላጎትና ጥቅም ማገልገል ነው።

በእንዲህ አይነት እኩይ ድርጊት የተሰማሩትን አረመኔዎች መላው ህዝብ እና መንግስት በተባበረ ክንድ ሁሉንም አማራጮች ተጠቅመው ስርዓት እንዲይዙ ያደርጋሉ። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሁሉም ይስተካከላል። እየነፈሰ ያለው ሰላምም ይፀናል።

ዘገባው የኢዜአ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *