የግብርና ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል- ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብር ቢሮ በምግበ ስረዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ትብብር በካፋ ዞን፣ አዲዮ ወረዳ በኖራ የታከመ የመኸር ስንዴ ማሳ የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል።

በክልሉ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በአርሶአደሩ ማሳና በማሰልጠኛ ተቋማት በምርምር በመታገዝ እና የተሞላ ግብዓትን በመጠቀም የተጀመረው ተግባር አበረታች ውጤት እያሳየ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በጉብኝታቸው ወቅት የገለጹት።

የተጎዱ መሬቶችን በኖራ በማከም የተጀመረው ተግባር ውጤታማ በመሆኑ ምርት በተሻለ ይዞታ ላይ መሆኑን መመልከታቸውን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ የግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል ኖራን አንደ አንድ የግብርና ግብዓት በተሟላ መልኩ መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል።

በክልሉ በአብዛኛው አካባቢ የዝናብ ሁኔታ ከመደበኛው ከፍ ያለ በመሆኑ አፈር እተየሸረሸረ ጠቃሚ ነጥረ ነገሮች የሚታጠቡበት ሁኔታ ያለ በመሆኑ ኖራን መጠቀም አስገዳጅ እየሆኑ በመሆኑ በቀጣይም የኖራ አቅርቦት በማሳለጥ በልዩ ትኩረት መሰራት እንደሚገባም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት።

በክልሉ በ2016/2017 መኸር ከ340ሺህ በላይ ማሳ በመኸር ምርት መሸፈኑን ከዚህም ውስጥ 100ሺህ የሚጠጋው ማሳ በኩታ ገጠም የለማ መሆኑን በመግለጽ ይህም አጠቃላይ ለእርሻ ስራና ለግብዓት አጠቃቀም እንዲሁም ምርትን ለመወጣት አመቺ እንደሆነም ነው ያብራሩት።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው በምርት ዘመኑ ከ1500 በላይ ሄክታር አሲዳማ አፈር በማከም ለእርሻ ስራ ምቹ የማድረግ ተግባር መሰራቱን ገልጸዋል።

በኖራ በታከመው መሬት ላይ ውጤታማ ምርት መገኘቱን የገለጹት አቶ ማስረሻ ተግባሩ በክልሉ ሁሉም አከባቢዎች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል።

የተጎዱ መሬቶችን በኖራ ማከምና የግብርና ግብዓት በአግባቡ በመጠቀም ምርትና ምርታማነት ማሻሻል አስፈላጊ በመሆኑ ለቀጣይ የምርት ዘመን ተሞክሮ የሚቀመርበትም መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

በክልሉ አብዛኛው የእርሻ መሬት የተጎዳ በመሆኑ በኖራ ማከም ምርታማነትን ለመጨመር አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት በክልሉ ግብርና ቢሮ የአፈር ልምነት ማሻሻያ ዳይሮክተሬት አቶ አምኖ መሀመድ

በተለያዩ አካባቢዎች የኖራ ምርት አለኝታ ጥናት በማድረግ የተሻለ የምርት ክምችት ማግኘት መቻሉንና በቀጣይ ለአርሶአደሩ በስፋት ተደራሽ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በግብርናው ዘርፍ የተጀማመሩ ተስፋ ሰጪ ተግባራት ውጤታማ በመሆኑ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ የገለጹት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በዞኑ አሲዳማ አፈርን የማከምና ለግብርና ስራ ምቹ የማድረግ ስራ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በመስክ ጉብኝቱ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፌ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ከክልሉ ሁሉም አከባቢዎች የመረጡ ሞዴል አርሶአደሮችና የግብርና ባለሙያዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *