




የሸካ ዞን ጤና መምሪያ የእናቶች ህፃናትና የስርዓተ ምግብ ዳይረክቶሬት የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 8 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት አፈፃፀም ግምገማ በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
የሸካ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ እምሩ ወዬሳ መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ እንደተናገሩት መንግስት የጤና ዘርፍ ማጠንጠኛው የእናቶችና ህፃናትን ጤና ማስጠበቅ ሲሆን ለዚህ ተግባር መሳካት የባለድርሻ አካላት ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።
በአለማችን ደረጃ ዋናነት ለእናቶች ሞት ምክንያት የሆነው የማህፀን በር ካንሰር በመሆኑ ዕድሜያቸው ከ 9 ዓመት በላይ የሆኑ ህፃናትን በማስከተብ በሽታውን ለመከላከል መረባረብ ያስፈልጋል ሲሉም ገልፀዋል።
በተለያዩ ጊዜያት ዕድሜያቸው ለክትባት የደረሱ ህፃናት ሆኖ ክትባት ያልወሰዱትን ለይቶ ድጋሜ ክትባት ለመስጠት የሚያግዝ አሰራር ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ያስፈልጋልም ብለዋል።
5ኛ ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከቀን 18/7/2018 ጀምሮ በመደበኛና ቤት ለቤት ስለሚሰጥ ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን በማስከተብ ህፃናትን ከበሽታው እንዲታደጉም አሳስበዋል።
አቶ እምሩ አክለውም በዘመቻው ትኩረት ከሚደረግባቸው ጉዳዮች ዋነኛው የአፈጣጠር ችግር ያለባቸው ህፃናት በመለየት ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የህፃናትን ጤና ለመጠበቅ ዋናው ማጠንጠኛው የህፃናት ክትባትን ወቅቱን ጠብቅ መስጠት በመሆኑ ለተግባር ስኬት ልዩ ተኩረት ይሻል ነው ያሉት።
የዕድገት ክትትልና የስርዓተ ምግብ ማተኮሪያው የህፃናትን መቀንጨር ለመከላከል በመሆኑ አሁን በአንዳንድ አካባቢዎች የሚከሰተውን መቀንጨር ለመከላከል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይሻል ብለዋል።
መደበኛ ክትባት ማጠናከሪያው ከአንድ ዓመት በታች ለሆኑ ጨቅላ ህፃናት የሚሰጥና ከአንድ አመት እስከ አምስት ዓመት ለሆኑ ህፃናት እንደሆነም ተገልጿል።
በመድረኩ የመምሪያው የእናቶችና ህፃናት ጤናና የስርዓተ ምግብ ዳይሬክቶሬት የ2018 በጀት ዓመት የተግባር አፈፃፀም ሪፖርት በመምሪያው የእናቶችና ህፃናት አስተባባሪ በአቶ ተገኝ ገቦ እየቀረበ ይገኛል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
