




በቤንች ሸኮ ዞን በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር በወንዞች ምክንያት ሲስተጓጎሉ የቆዩ የትራንስፖርት ችግሮችን ለመፍታት፣ ከ67 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነቡ የሦስት ድልድዮች የመሰረት ድንጋይ የመቀመጥ ስነ-ስርዓት ተካሂዷል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን ባስተላለፉት መልዕክት፣ የብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት የህዝብን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
በተለይም በኮሪደር ልማት፣ በሌማት ትሩፋት እና በተለያዩ የልማት ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፣ “ከተማ ሲያድግ ገጠሩም አብሮ ያድጋል” በሚል እሳቤ የሚዛን አማን ከተማን ተመራጭ የኢኮኖሚና የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
አያይዘውም፣ መጪው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ነዋሪው የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን በበኩላቸው፣ የከተማው ነዋሪ ሲያነሳቸው የቆዩ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች በመንግስትና በፓርቲው ተገቢው ምላሽ እየተሰጣቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ዞኑ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰባቸውን ፕሮጀክቶች እያከናወነ መሆኑን የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው፣ ከ1.8 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት መዘጋጀቱንም እንደ ማሳያ አንስተዋል።
የሚዛን አማን ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ሰለሞን ሌዊ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠላቸው ድልድዮች የዊይኒ ወንዝ፣ የኪ 1 እና የኪ 2 ላይ የሚገነቡ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ማህበረሰቡ ለልማቱ በሰጠው ትዕግስትና በከፈለው መስዋዕትነት ልክ ጥራት ያለው ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል ብለዋል።
ከተማዋን የቀድሞ ታላቅነቷንና የንግድ ማዕከልነቷን ለመመለስ ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለጹት ከንቲባው፣ ከድልድይ ግንባታው በተጨማሪ የአማን ጤና ጣቢያ ምረቃም በእለቱ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ በተለይ የህዝብ ጥያቄ የነበሩ የደም ባንክ እና የኦክስጅን ፕላንት ግንባታን በማከናወን የጤና ችግሮችን መፍታት፤ በትምህርት ዘርፍ በ20 ቀናት ውስጥ ትምህርት ቤት የመገንባት አርዓያነት ያለው ስራ፤
ከተማዋን የኢኮኖሚና የመዝናኛ ማዕከል ለማድረግ የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች መሰራታቸው ተመላክቷል።
በመጨረሻም፣ በዘንድሮው ዓመት ብቻ በርካታ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ተጀምረው ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸው የከተማዋን ፈጣን እድገት የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል ሲል የከተማው ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
