ጤናማ የሆነ የስርዓተ ምግብ አጠቃቀምና መደበኛ የሆነ ክትባት ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተገለፀ

Spread the love

‎የሸካ ዞን ጤና መምሪያ የእናቶች ህፃናትና የስርዓተ ምግብ ዳይረክቶሬት የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 8 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት አፈፃፀም ግምገማ በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

‎የሸካ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ እምሩ ወዬሳ መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ እንደተናገሩት መንግስት የጤና ዘርፍ ማጠንጠኛው የእናቶችና ህፃናትን ጤና ማስጠበቅ ሲሆን ለዚህ ተግባር መሳካት የባለድርሻ አካላት ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።

‎በአለማችን ደረጃ ዋናነት ለእናቶች ሞት ምክንያት የሆነው የማህፀን በር ካንሰር በመሆኑ ዕድሜያቸው ከ 9 ዓመት በላይ የሆኑ ህፃናትን በማስከተብ በሽታውን ለመከላከል መረባረብ ያስፈልጋል ሲሉም ገልፀዋል።

‎በተለያዩ ጊዜያት ዕድሜያቸው ለክትባት የደረሱ ህፃናት ሆኖ ክትባት ያልወሰዱትን ለይቶ ድጋሜ ክትባት ለመስጠት የሚያግዝ አሰራር ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ያስፈልጋልም ብለዋል።

‎5ኛ ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከቀን 18/7/2018 ጀምሮ በመደበኛና ቤት ለቤት ስለሚሰጥ ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን በማስከተብ ህፃናትን ከበሽታው እንዲታደጉም አሳስበዋል።

‎አቶ እምሩ አክለውም በዘመቻው ትኩረት ከሚደረግባቸው ጉዳዮች ዋነኛው የአፈጣጠር ችግር ያለባቸው ህፃናት በመለየት ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

‎የህፃናትን ጤና ለመጠበቅ ዋናው ማጠንጠኛው የህፃናት ክትባትን ወቅቱን ጠብቅ መስጠት በመሆኑ ለተግባር ስኬት ልዩ ተኩረት ይሻል ነው ያሉት።

‎የዕድገት ክትትልና የስርዓተ ምግብ ማተኮሪያው የህፃናትን መቀንጨር ለመከላከል በመሆኑ አሁን በአንዳንድ አካባቢዎች የሚከሰተውን መቀንጨር ለመከላከል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይሻል ብለዋል።

‎መደበኛ ክትባት ማጠናከሪያው ከአንድ ዓመት በታች ለሆኑ ጨቅላ ህፃናት የሚሰጥና ከአንድ አመት እስከ አምስት ዓመት ለሆኑ ህፃናት እንደሆነም ተገልጿል።

‎በመድረኩ የመምሪያው የእናቶችና ህፃናት ጤናና የስርዓተ ምግብ ዳይሬክቶሬት የ2018 በጀት ዓመት የተግባር አፈፃፀም ሪፖርት በመምሪያው የእናቶችና ህፃናት አስተባባሪ በአቶ ተገኝ ገቦ እየቀረበ ይገኛል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *