
በ NABU ኢትዮጵያ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ማስተባበሪያ ጸህፈት ቤት በቡና መረጃ መሰብሰቢያ መተግበሪያ ዙሪያ የአሰልጣኞች ስልጠና በቦንጋ ከተማ እየሰጠ ነው።
ስልጠናውን በመልዕክታቸው ያስጀመሩት የክልሉ ግብርና ቢሮ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ መላኩ፤ የሀገራችን ኢኮኖሚ መሠረት ከመሆኑም ባሻገር በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ መሆኑን ጠቁመዋል።
ክልሉ የቡና ምርታማነትና ጥራትን የሚያሳድጉ የተለያዩ ምርምሮችን በማድረግ በዓለም ዐቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ፣ ዱካውና የምርት ሂደቱ የሚታመን ምርት ለማቅረብ የተቀናጀ ስራ እየተሰራ መሆኑን አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል።
የሀገሪቱ መንግስት ከአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ፍላጎት መሰረት የተዘጋጀው ከደን ጭፍጨፋ ነፃ ምርት (EUDR) ደንብ ወደ ትግበራ ከገባ በኃላ የታየውን አወንታዊ ለውጦች ለማስቀጠልና ክፍተቶችን ለመሙላት ስልጠናው አይነተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
ስልጠናው የቡና ምርትን በዓለም ገበያ ላይ እንዲቆይ የሚያደርግ ተሰሪካዊ ኃላፊነት ስለሆነ በልዩ ትኩረት እንዲወስዱ አሳስበው NABU ኢትዮጵያ ለክልሉ ቡና ልማት ለሚያበረክተው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የ NABU ኢትዮጵያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አሳዬ አለማየሁ፤ ፕሮጀክቱ የቡና ጫካን መሰረት አድረጎ የመጣ ከመሆኑም በላይ የተለያዩ ደኖችና በውስጡ ያሉ ሀብቶችን በባዮስፌር ማስመዝገቡን አውስተዋል።
ስልጠናው በፌደራል ቡናና ሻይ ባለስልጣን የተዘጋጀውን የቡና መረጃ መሰብሰቢያ መተግበሪየሰ (ECTMS App) አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ሲሆን እንደ ሀገር የቡና ጫካ ማዕከል የሆነውን ክልላችን የቃኘ ነው ብለዋል።
በስልጠናው ላይ 6ቱ የፕሮጀክቱ ወረዳ ተወካዮች፣ የክልሉ ቡናና ሻይ ባለስልጠን ባለሙያዎች፣ የክልሉ ግብርና ባለሙያዎችና አመራሮች፣ በክልሉ ያሉ የቡና ዩኒዬኖችና ሌሎች ሻለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።
በአሻግሬ ገብረወልድ
