

በአገር አቀፍ ደረጃ እስካሁን ባለው ሂደት 12 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመኸር ሰብል መሸፈኑን የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ገለፁ።
2016 በጀት ዓመት ከግብርና ግብዓት ስርጭት ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮችን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለመቅረፍ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር የ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም እና የ2016 ዓ.ም በጀት ዕቅድ ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡
በመድረኩ የእርሻና ሆልቲካልቸር፣ የእንስሳት እና ዓሳ ኃብት እንዲሁም የተፈጥሮ ኃብት ልማት ዘርፎች ላይ የአፈጻጸም ሪፖርትና የቀጣይ እቅድ ቀርቦ ምክከር ተደርጎበታል።
በመድረኩም የግብርና ሚኒስቴር፣ የክልል ግብርና ቢሮ፣ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አመራሮች እንዲሁም የሌሎች ባለድርሻ ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና ተወካዮች ተገኝተዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በዚሁ ጊዜ በ2015 በጀት ዓመት በዋና ዋና የግብርና ልማት ስራዎች ላይ ውጤታማ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በእንስሳት እና አሳ ሃብት ልማት ላይ የተሻለ ስራ መከናወኑን ገልጸው፤ በሌማት ትሩፋት ላይ ጥሩ ጅማሮ ታይቷል ነው ያሉት፡፡
የስንዴ ምርትን ከውጭ ማስገባት ሙሉ በሙሉ ከማቆም ባሻገር ለውጭ ገበያ ማቅረብ የተጀመረበት ዓመት እንደነበርም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በግብርናው ዘርፍ ላይ የተመዘገበው ውጤት በሌሎች ዘርፎች ላይ መነቃቃት የፈጠረ ስለመሆኑም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በ2015 በጀት ዓመት አሲዳማ አፈር በማከም ረገድ ግን በሚፈለገው ደረጃ እንዳልተሰራ ጠቁመዋል፡፡
በግብርና ግብዓት አቅርቦት ላይ ችግሮች መስተዋላቸውን አንስተው፤ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና ህገወጥነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በበጀት አመቱ በዘርፉ ለታየው ስኬት የግብርና ባለሙያዎች፣ አመራሮች እና ባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ ነበር ብለዋል።
የ2016 በጀት ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በእንስሳት እና አሳ ሃብት ልማት እና የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብርን ማጠናከር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ በግብርና ግብዓት አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራም እንዲሁ፡፡
ለዚህ ደግሞ የአፈር ማዳበሪያ ግዥን ቀደም ብሎ ከማከናወን ባለፈ ስርጭቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለመቆጣጠር እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
በ2016 መኸር ወቅት 17 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስካሁን ባለው ሂደት 12 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በመድረኩ ከተገኙት የክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ስሩር፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በዘርፉ የተመዘገቡ ውጤቶችን በቀጣይ ይበልጥ ለማጠናከር በቅንጅት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው በበኩላቸው በቀጣይ ክልሉ ለግብርና ልማት ያለውን አቅም በአግባቡ ለመጠቀም እንደሚሰራ ነው የተናገሩት ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
