
በአማራ ክልል እየተከናወነ ያለው የሕግ ማስከበር ተግባር በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ክልሉን ወደ ሰለማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ አስታወቀ።
በአማራ ክልል ያጋጠመውን የፀጥታ መደፍረስ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ የፌዴራል መንግሥት አስፈላጊውን የሕግ ማዕቀፍ እንዲተገብር የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መጠየቁ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲተገበር በሙሉ ድምፅ ያጸደቀ ሲሆን፤ አዋጁን የሚያስተባብር ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።
በዛሬው ዕለትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መመሪያ ዕዝ ችግሩን ለመፍታት ያዘጋጀውን ዕቅድ አፈጻጸም በሚመለከት ውይይት አድርጓል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መመሪያ ዕዝ ዋና ሰብሳቢ አቶ ተመስገን ጥሩነህ በሰጡት መግለጫ፤ በክልሉ በተደራጁ ዘራፊ ቡድኖች የተከሰተው የሰላም መደፍረስ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና አስተዳደራዊ ችግሮችን ፈጥሯል ነው ያሉት።
ዘራፊ ቡድኖች የሕዝብ አግልግሎት መስጫ ተቋማት አገልግሎት እንዳይሰጡ ከማስተጓጎል ባሻገር በአንዳንድ አካባቢዎች ማረሚያ ቤቶችን ሰብረው ወንጀለኞችን እንዲያመልጡ እስከማድረግ የደረሰ ውንብድና መፈጸማቸውን ጠቁመዋል።
ይህም በተለይ የክልሉ አርሶ አደር የመኸር እርሻ ወቅትን ተረጋግቶ እንዳያከናወን ማድረጉን ጠቅሰው፣ ዜጎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው አገልግሎት እንዳያገኙ ማድረጉን ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ በክልሉ የተከሰተውን የፀጥታ መደፍረስ ለመቀልበስ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዘራፊ ቡድኑ የሕዝብ መገልገያ ተቋማትን በመዝረፍ እና በማውደም ጭምር የክልሉ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ በደል እየፈጸመ መሆኑንም ገልጸዋል።
መንግሥት የትኛውም ጥያቄ በሰላም መፈታት እንዳለበት በጽኑ ያምናል፤ ባለፉት ጊዜያትም ይህንን በተግባር አሳይቷል ብለዋል።
በቀጣይ መንግሥት ሕግ እና ሥርዓት የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጭምር ነው የተናገሩት።
በክልሉ እየተከናወነ ያለው የሕግ ማስከበር ሥራ በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ክልሉን ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን እንዲቆም እና ሰራዊቱን እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
