






የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የጤና ቢሮ ከክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ሀገር አቀፍ የ4ኛ ዙር የፖሊዮ ዘመቻ አፈጻጸም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቦንጋ እየገመገመ ይገኛል።
ግምገማ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃፊው አቶ ኢብራሂም ተማም የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በክልሉ ሁሉም አካባቢ መሰጠቱን ገልጾ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገው ርብርብ ከ100% ህፃናት መከተቡን በላይ አፈጻጸም መመዝገቡን አንስተዋል።
የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ወቅት በቅንጅት በተሰራው ስራ የስርዓተ ምግብ ችግር ልየታ በነፍሰጡር፣ የሚያጠቡ እናቶችና ህፃናት መለየት መቻሉን በማንሳት የተለዩ ህፃናትን ከህክምና ተቋማት ጋር ከማስተሳሰር የቀጣይ ትኩረት እንደሚሻ አንስተዋል።
ባለፉት ዓመታት በቅንጅት በተሰራው ዘርፌ ብዙ ስራ በወባ በሽታ ከመከላከልና መቆጣጠር አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ያወሱት አቶ ኢብራሂም አሁንም ጫና ባለባቸው አካባቢዎች በልዩ ትኩረትና በቅንጅት መሠራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተሰራው የዘመቻ ስራ የተሻለ ውጤት መምጣቱን በማንሳት ከዚህ ተሞክሮ በመቀመር በመደበኛው ተግባር በሚከናወኑ የጤና ተግባራት በቀጣይ ትኩረት በመስራት እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል።
የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት በቢሮው የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወሰን ጨምሳ 4ኛ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
4ኛ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ጎን ለጎን የተለያዩ የጤና ተግባራት በቅንጅት መመራቱን በማንሳት በዘመቻው የተገኙ ተሞክሮዎችን ለማላቅና ጉድለቶችን በመለየት ለግብዓት በመውሰድ ለተሻለ ውጤት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አቶ ወሰን ተናግረዋል።
የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ እና የተቀናጀ የጤና ተግባራት አፈጻጸም ሰነድ በቢሮው የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ዳይረክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋጽዮን ተረፈ ለተሳታፊዎች እየቀረበ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የዞን ጤና መምሪያ እና የወረዳ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች፣ የአራቱ ኤፍ ኤም ስራ አስኪያጆች፣ የክልሉ
ጤና ቢሮ ማኔጀመንትና ባለሙያዎች እና ሌሎች የባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በጌታሁን ግርማ
