





የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ፖሊስ ኮሚሽን በሞዲዮ ፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም ለሶስተኛ ጊዜ ያሰለጠናቸው የመካከለኛ እና ከፍተኛ ማዕረግ ሽግግር ሰልጣኝ የፖሊስ መኮንኖችን አስመረቀ።
ተመራቂዎቹ የቆይታ ጊዜያቸዉን የሸፈኑ ከዋና ሳጅን ወደ ረዳት ኢንስፔክተር እና ከኢንስፔክተር ወደ ዋና ኢንስፔክተር ሽግግር የሚያደርጉ ናቸው።
በምረቃው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እንደገለጹት ፤ የፖሊስ ሠራዊትና የጸጥታ መዋቅር ዋነኛ ሚና ህገመንግስት እና ህገመንግስታዊ ሥርዓትን መጠበቅና ማስጠበቅ ነው።
ዛሬ የተመረቃችሁ የመካከለኛ እና ከፍተኛ የማዕረግ ሽግግር ያደረጋችሁ የፖሊስ መኮንኖች ህገመንግስት እና ህገመንግስታዊ ሥርዓት ፣ ሰብዓዊ መብት አጠባበቅ፣ በወንጀል መከላከል፣ በፖሊስ ሠራዊት ሥነምግባርና በሌሎች ጉዳዮች በሸመታችሁና ባካበታችሁ ዕውቀት ካለፈዉ ጊዜ በተሻለ ህዝብና መንግሥትን ማገልገል አለባችሁም ብለዋል።
ሀገራችን ባለፉት ጊዜያት የውጭና ውስጥ ጫናዎችና ፈተናዎች ቢደነቁባትም በፖሊስ ሠራዊትና በጸጥታ መዋቅር ጠንካራ ጠባቂዎች በኩራትና በድል እየተሻገረች የማንሰራራት ጉዞ መጀመሯን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት።
በሀገር ደረጃም ብሎም በክልላችን የተጀመረው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዞ እንዲሁም ሠላምና ጸጥታ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የፖሊስ ሠራዊት አባላትና ጸጥታ ተቋማት ሚናቸውን በተገቢው እንዲወጡም አሳስበዋል ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)
በዚህም እንደሀገር የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ማደናቀፍና የመንግስት ሥልጣን በኃይል ለመቆናጠጥ የሚፈልጉ አካላትን የማክሸፍ እና የመከላከል ኃላፊነት እንዲወጡም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በፖሊስ ተቋማት ዘንድ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት እና የጀመረውን የሪፎርም ሥራ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን የክልሉ መንግስት ያለሰለሰ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል በንግግራቸው።
በክልሉ የተጀመረው አዎንታዊ ሠላምና ጸጥታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የፖሊስ ተቋም የመደገፍና የማገዝ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም የክልሉ ሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አለሙ ናቸው የተናገሩት።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ፈቀደ በቀለ በበኩላቸው፤ ከለውጡ ወዲህ የህዝቡን ደህንነት ለመጠበቅና ሠላማቸውን ማረጋገጥ የሚያስችል የሪፎርም ሥራዎች በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
እንደሀገር የተጀመረው የሪፎርም ሥራ ውጤታማ እንዲሆን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በአጭር፣ መካከለኛ እና በረዥም ጊዜ የፖሊስ አባላት አቅም ለመገንባት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛልም ብለዋል።
ኮሚሽኑ በፖሊስ አባላት ዘንድ በየጊዜው ሲነሳ የነበረው የማዕረግ ሽግግር ፣ የአቅም ግንባታ እና ሌሎች የጥቅማጥቅም ጥያቄዎችን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የገለፁት ኮሚሽነሩ ተግባሩ በቀጣይነት ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።
በፍቅር ከበደ
