






የፌደራል ገቢዎች ሚንስተር ጂማ ቅርንጫፍ ከክልሉ ገቢዎች ቢሮና ኅብረት ስራ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በክልሉ ለሚገኙ ዩንየን ቦርድ ሰብሳቢዎች፣ስራ አስኪያጆች እንዲሁም ባለሙያዎች በታክስ አስተዳደር አዋጆችና ድንጋጌዎች ላይ ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ ስልጠና ነክ የውይይት መድረክ በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነው።
የዕለቱ የክብር እንግዳ እና የክልሉ ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቀበሌ መንገሻ ባስተላለፉት መልእክት፣መንግስት ገቢን በተለያዩ መንገድ እየሰባሰበ መልሶ ለሀገር ልማት ለማዋል የገቢ መሰረቶችን በማስፋት ከተለያዩ ዘርፎች ገቢን ማሰባሰብ የሚየስችሉ የገቢና ታክስ አዋጆች ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።
በገቢ ግብርና ታክስ አስተዳደር አዋጆችና ድንጋጌዎች በህብረት ስራ ማህበራት አዋጆችና ደንቦች መካከል ለህብረት ስራ ማህበራት ስለግብርና ታክስ አከፍፈል የተሰጣቸዉ መብትና ግዴታ መካከል በተፈጠረዉ የግንዛቤ ክፍተት ምክንያት በክልላችን ባሉ ሕብረት ስራ ማሕበራት በገቢ ተቋም ኦዲት ከተደረጉና የኦዲት ዉጤት ከደረሳቸዉ በኋላ ተመልሰዉ እንደማህበር የሚቀጥሉ ሳይሆን ያፈሩትን ሀብት ከመሸጥም ባለፈ ስራ አቁመዉ እስከመተን የደረሱ ማህበራት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።
የማህበራትና ዬንየኖች ከስራ ዉጭ መሆንና መበተን በአባለት ኑሮና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ እያሳደረ ያለዉ ተጽዕኖ የከፋ እየሆነ መምጣቱን በመግለፅ እነዚህንና መሰል ችግሮች ላይ በጋራ ተወያይቶ ለቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ መፍታት እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።
በመሆኑም የዛሬዉ መድረክ የፌደራል ገቢዎች ሚኒስተር ጂማ ቅርንጫፍ በቅርበት ከክልሉ ገቢዎች ቢሮ ጋር እየሰራ እንደመሆኑ መጠን በክልሉ ለሚገኙ የዩንየን አመራሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ለመስጠት መድረኩ መመቻቸቱን ጠቁመዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ህይወት አሰግድ ባደረጉት ንግግር ዘመናዊ የገቢ አሰባሰብ ስርዓት በመዘርጋት የገቢ አሰባሰብ አቅም ማሳደግ እንደሚገባ አስረድተዋል።
የሚደራጁ ማህበራት ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክቱትን ድርሻ ለማሳደግ ጠንካራ ዪኒየኖችን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑ ገልጸዋል።
በመድረኩም የህብረት ስራ ማህበራት እና የዩኒየኖች ታክስ አሰባሰብና አስተዳደር ላይ የተዘጋጀ የስልጠና ሰነድ የፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር የጂማ ቅ/ታክስ ዘርፍ ኃላፊና አቶ ነጋሶ አብዲሳ እየቀረበ ይገኛል።
በካሳሁን አሰፋ
