



ሀገራዊ ለውጡ እውን የሆነበት 8ኛ ዓመትና የመጋቢት 24 ታሪካዊ ድሎች የሚዘከሩበት ደማቅ የሕዝባዊ ድጋፍ ሰልፍ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል ።
ሰልፉ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡ ተጨባጭ የልማት ውጤቶችን ለማስታወስና ዕውቅና ለመስጠት ያለመ ነው።
በዕለቱ አስተያየታቸውን የሰጡ በክልሉ የካፋ ዞን፤ ቦንጋ ከተማ ወጣቶች፣ የለውጡ መንግስት እያመዘገባቸው ያሉት ውጤቶች “በብርሃን የሚታዩና የሚጨበጡ” መሆናቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ የተመዘገቡ የለውጡ ትሩፋቶች ለተሻለ ነገ ተስፋ የሚሰጡ እንደሆናቸው ነው ወጣቶች የገለጹት።
ወጣቶች በሀገሪቱ የመጡ ለውጦችን ለማስቀጠል በአንድነት እንደሚቆሙም ተናግረው፤ ወጣቱ ከልማቱ፣ ከእድገቱና ከሰላሙ ጎን መሆን ለነገው ስኬት ብቸኛው አማራጭ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የለውጡ መንግስት ለወጣቱ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያደረገ ያለው ድጋፍ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ ወጣቶችም ለለውጡ ስኬት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።
እንደወጣቶቹ ገለጻ፤ ሁሉም ወጣቶች ራሳቸውን ከሀሰተኛ መረጃዎች እንዲጠብቁና በመንግስት የተፈጠሩ ዕድሎችን በተገቢው መጠቀም አለባቸውም ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የለውጡ መንግስት ያስጀመራቸውን የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል አስተያየት ሰጪ ወጣቶች።
ወጣቶችም ይህ የድጋፍ ሰልፍ ወጣቱ ለሀገራዊ አንድነትና ለልማት ያለውን ቁርጠኝነት ዳግም ያረጋገጠበት ነው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በፍቅር ከበደ
