




ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እያካሄደ ያለው ምክክር ኢትዮጵያውያን ተነጋግረው የራሳቸውን ችግሮች ራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ ማረጋገጫ ሊሆን እንደሚችል ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገ/ማርያም ተናገሩ።
እርሳቸው የተሳተፉበት የፌዴራል ተቋማት እና ማኅበራት የምክክር መድረክ ተሳተፊዎች ሀሳባቸውን ያለገደብ ማንሳታቸውንም ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ጠቅሰዋል።
በመድረኩ ላይ ሲሳተፉ የዳያስፖራውን ጉዳይ በስፋት ማንሳታቸውን ጠቅሰው፤ ዳያስፖራው የሀገር ኢኮኖሚን በመደገፍም ሆነ ሀገርን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላለው በምክክሩ እንደ አንድ የማኅበረሰብ አካል አጀንዳው ሊያዝለት ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ እስካሁን ከዚህ የማኅበረሰብ ክፍል የሚገባትን መጠቀም እንዳልቻለች ጠቅሰው፤ የዳያስፖራው አጀንዳ ወደ ፊት መጥቶ ለሀገር የሚጠቅመውን ሁሉ ማበርከት እንዲችል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።
በምክክር መድረኩ በርካታ ሃሳቦች እንደተነሱ የጠቀሱት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ፥ የተነሱት ሀሳቦች ብንነጋር የችግሮቻችን ምንጮች ጥቂት መሆናቸውን አመላካቾች ናቸው ብለዋል።
በመነጋገር ለማንኛውም ጉዳይ መፍትሔ ማምጣት ይቻላል የሚሉት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ፤ በጦርነት ያልሞከርነው ነገር ስለሌለ ያልሞከርነውን የምምክር መንገድ ላይ መሥራቱ ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ይረዳል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ ሁሉ ጊዜ ወስዶ ሲነጋገር የተገነዘብነው ነገር መነጋገር ቢቻል ኖሮ አጨቃጫቂ ተብለው የተነሱት ጉዳዮች ሁሉ ለግጭቶች መንሰኤ ሊሆኑ አይገባ እንደነበር ነው ብለዋል።
እነዚህ ለዘመናት ሲያጨቃጭቁን የነበሩ ጉዳዮች ቁጭ ብለን ብንወያይባቸው እንዲሁም ለሕዝብ ቀርበው ንግግር ቢደረግባቸው ኖሮ እስከ ዛሬ እንደሀገር የከፈልነውን ያልተገባ ዋጋ አንከፍልም ነበርም ነው ያሉት።
መድረኩ እየፈጠራቸው ያሉ ተከባብሮ የመደማመጥ ባህል እንደ ሀገር ሊያድግ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ይህ ባህል ሲዳብር ኢትዮጵያን ወደ ታላቅነቷ መመለስ ይችላልም ብለዋል ፕሮፌሰር ዓለማየሁ።
ኢትዮጵያውያን ቂም በቀልን ሳያሳድሩ ችግሮቻቸውን የሚፈቱባቸው መልካም ባህሎች እንዳሏቸውም አንስተው፤ እነዚህን መልካም የችግር መፍቻ ባህሎቻችንን ወደ ፊት በማምጣት ከግጭት አዙሪት ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
በተሳትፏቸው አጋጣሚ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ድምጽ በነጻነት እንዲሰማ እያደረገ መሆኑን እንደተረዱ ጠቁመው፤ ከዚህ በታቃራኒ የሚራገበው አሉባልታ ግን መሰረት እንደሌለው ገልጸዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
