



በዉይይቱ የተሳተፉ የጤና ባለሙያዎች በሰጡት አስተያየት የእነሱን ሚዛናዊ ጥያቄ ለፖለቲካ ዓላማ ለማዋል የሚጠቀሙ አካላት ትክክል እንዳልሆነ ገልጸዉ ከሙያዉ ሥነ ምግባር ባፈነገጠ መልኩ በአንዳንድ ጤና ባለሙያዎች የሚታይ የስራ ማቆም እንቅስቃሴ ትክክል አለመሆኑን ገልጸዋል።
ለጤና ባለሙያዎች የተለያዩ የማትጊያ ስልቶችን በማበጀት የጤና ባለሙያዎችን ማበረታታት እንደሚገባ የገለጹት ተሳታፊዎቹ፥ ለጥቅማጥም ጥያቄያቸውም በየደረጃዉ ያለዉ የመንግሥት መዋቅር ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
የጤና ተቋማትን በቁሳቁስና በብቁ የሰው ሀይል በማደራጀት የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል እንደሚገባ ያሳሰቡት ተሳታፊዎቹ የክልሉ መንግሥት የጤና ባለሙያዎችን መሠረታዊ ጥያቄ በውይይት ለመፍታት ያሳየው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መኾኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የሪፈራል ሆስፒታል ያለመኖር እንዲሁም የመድኃኒት አቅርቦትን የሚያሳልጥ ማዕከል ባለመኖሩ አግልግሎት ለማግኘት ህብረተሰቡ ለአላስፈላጊ ወጪ እየተዳረገ በመሆኑ ቀጣይ ትኩረት እንዲሰጠውም ጠይቀዋል።
የጤናው ዘርፍ ተግዳሮቶች በመቅረፍ የአገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን የክልሉ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን የገለጹት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በየደረጃው ያለው መዋቅር በጤና ተቋማት የግብዓት አቅርቦት በማሳለጥ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በጤና ባለሙያዎች ለተነሳው የመብት ጥያቄ የፌዴራል መንግሥት በጥናት ምላሽ ለመስጠት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ በክልል ደረጃ የሚፈቱ ጥያቄዎችን በቀጣይ አጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የጤና ባለሙያዎች ማትጊያ፣ የሥራ ላይ ስልጠና እና ሌሎች የአቅም ግንባታ ስራዎች በቀጣይ በትኩረት እንደሚከናወን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ከመኖሪያ ቤት ግንባታ መሬት በተከሞች በመደራጀት እንዲያገኙ እንደሚገባም ነው የገለጹት።
የጤና ባለሙያዎች በችግር ጊዜ ከህዝባቸው ጎን በመሆን አግልግሎት ለአፍታም እንዳይቋረጥ በማድረግ ላሳዩት የሙያ ስነ-ምግባር እና ሰብዓዊ ተግባር ክብር እንደሚገባው የገለጹት የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል መዳበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የክልሉ መንግሥት የዘርፉን ችግር ደረጃ በደረጃ በመፍታት ማህበራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በትጋት እንደሚሰራ የገለጹት አቶ ፍቅሬ በክልሉ ያደረ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ያሉበት በመሆኑ በጋራ አረዳድ ችግሮችን መፍታት ይገባል ብለዋል።
የጤና ባለሙያዎች የትምህርት እና ደረጃ ማሻሻያ በጤና ሪፎርም ማዕቀፍ ተገቢውን ምላሽ እንደሚያገኝ የገለጹት የክልሉ የጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም የባለሙያዎች የተጋላጭነት ማካካሻ ክፍያ ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ በጤና ሚኒስቴር ጥናት መጀመሩን ተናግረዋል።
የጤና አግልግሎት አሰጣጥ ችግር ለማሻሻል የክልሉ መንግሥት አቅም በፈቀደው ሁሉ እየደገፈ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ኢብራሂም በተላይ በልዩ ሁኔታ የአርብቶ-አደር አከባቢ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል።
በዕድገቱ በዛብህ
