


128ኛው የዓድዋ በዓል”ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል”! በሚል መሪ ቃል በቦንጋ ከተማ እየተከበረ ነው።
በክብረ በዓሉ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው የዓድዋ ድል በዓል የሕብረብሔራዊ አንድነት መገለጫ የጥቁር ህዝቦች በዓል ነው ሲሉ ተናግረዋል ።
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን የሕብረብሔራዊ ማህተማቸው ሆኖ የቆየ በዓል መሆኑንም ተናግረዋል ።
የማይቻለውን እንሚቻል ያረጋገጠ የታሪክ እጥፋት የተመዘገበበት የጥቁር ህዝቦች በዓል መሆኑንም በንግግራቸው አመላክተዋል ።
የዓድዋ ድል በዓል ኢትዮጵያን ያቆመ የወል ትርክታችን የኢትዮጵያዊያን የድል በዓል ነውም ሲሉ ተናግረዋል ።
ድሉን የሚያንጸባርቅ አሻራ እስካሁን እንዳልነበረ ያወሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የዓድዋ ድልን ሊመጥንና ሊዘክር የሚችል ዓድዋ 00 ኪሎሜትር መታሰቢያ ዘንድሮ ተገንብቶ መከበሩ የ128ኛውን የድል በዓል ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
የአሁኑ ትውልድ የጥንት አባቶቹን ታሪካዊ ድል በማስቀጠል በወል ትርክቶችና በጋራ እውነታዎች ላይ በመጽናት ሀገርን በሚያሻግር ተግባር መትጋት ይኖርባቸዋል ብለዋል ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ።
በክልሉ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን አሁን ላይ ያለውን ነጠላ ትርክቶችን በመተው የወል ትርክቶችን በማጽናት ሁሉም በተሰማራበት የስራ መስክ በመደመር እሳቤ ሀገር ተከብራና ታፍራ እንዲሁም በልጽጋ እንድትገኝ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል ።
የዓድዋን ድል የሚዘክር ኢትዮጵያዊነት የተባለ የኪነ ጥበብ ቡድን ተውኔት፣ሽለላና ቀረርቶ በዕለቱ አቅርበዋል።
“ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል”! በሚል መሪ ቃል በዶክተር መስፍን ወዳጆ አቅራቢነት ውይይት እየተደረገበት ነው።
በመድረኩ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣የካፋ ዞን አመራሮች፣የሀገር ሽማግሌዎች ፣የሀይማኖት አባቶች፣የክልልና የዞኑ የመንግስት ሰራተኞች፣የፖሊስ ሰራዊት አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ነው። በታጠቅ አበበ

