ካሳቫ የሚመደበው ከቁልቋል (Euphorbiaceae) ቤተሰብ ሲሆን ከ200 በላይ የሆኑ ዝርያዎች አሉት፡፡ ሳይንሳዊ ስያሜው (Manihot esculenta) ይባላል፡፡ በፖርቹጋል ነጋዴዎች አማካይነት መጀመሪያ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በቤንን ባህረሰላጤና በኮንጎ ወንዝ አድርጎ ወደ ምዕራብ አፍሪካ እንደ ገባ ይታወቃል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ 18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ በሪየኒየን፣ በማዳጋስካርና በዛንዚባር ወደቦች አድርጎ ወደ ምስራቅ አፍሪካ እንደ ገባ መዛግብት ያወሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ የካሳቫ ስርጭት እስከ 19ኛውና እስከ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ በጣም አዝጋሚ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ለምግብነት የሚውለውም ከመሬት በታች የሚገኘው ኮረቱ ነው ፡፡ ካሳቫ በሃይል ሰጪነቱ ከስራስር ተክሎች ሁሉ ተወዳዳሪ የሌለዉ ከምግብነት ጥቅሙ በተጨማሪ ለከብቶች መኖነት፣ ለእስታርች ኢንዱስትሪ ጥሬ እቃነት ተፈላጊ ነዉ፡፡
ካሳቫ በደቡብ ኢትዮጵያ የገባበት ትክክለኛ ዘመን ባይታወቅም ከ100 ዓመት በላይ እንደሆነ አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ካሳቫ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተከሰቱ ተደጋጋሚ ድርቆች የተነሳ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዳስፋፏቸው ይገመታል፡፡ ይሁን እንጂ በ1970ዎቹ አጋማሽ አካባቢ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በመልካሳና በመልካ ወረር ምርምር ማዕከላት የዝርያ መረጣ የምርምር ስራዎች እንደ ጀመሩና በኋላም በሃዋሳ ግብርና ምርምር ማዕከል በተደረጉ የምርምር ስራዎች በምርታቸውና በሌሎች ባህሪያቸው የተመረጡ ዝርያዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ መለቀቃቸውን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ የሆልቲካልቸር ሰብሎች ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተስፋዬ ገ/ሚካኤል ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የካሳቫ ሰብልን በስፋት ለማልማት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ የሆልቲካልቸር ሰብሎች ልማትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት የክልላችንን የምግብ ዋስትና ብሎ የአርሶ አደሩን የገቢ ምንጭ ከማሳደግ አንፃር በእንሰት ልማት፣ ከፍራፍሬ ሰብሎች ዉስጥ በሙዝና አቮካዶ እንዲሁም በአትክልትና ሥራሥር ሰብሎች በምርታመነት ላይ ሰፊ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል። በዚህ በተጨማሪም በክልሉ የካሳቫ ሰብልን በስፋት ለማልማት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተገልፀዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ብሎም በሌሎች አንዳንድ የአገሪቱ ክልሎች ለምግብነት ያለዉ ተፈላጊነት እየጨመረ በመምጣት ላይ ሲሆን የካሳቫ ዱቄቱ ለዳቦ፣ ለገንፎ፣ ለብስኩት ከጤፍ ጋር ለእንጀራና ወጥና ወዘተ… አገልግሎት ላይ እየዋለ ይገኛል ሲሉም አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡ ስለዚህ የሰብሉን ድርቅ የመቋቋም ባህሪውን፣በአነስተኛ መሬት ላይ ብዙ ምርት የመስጠት ችሎታውን እና ሌሎቸ ተፈጥሮአዊ ባህሪውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሰብሉን በተለያዩ የክልላችን አካባቢዎች ማስፋፋቱ ተገቢ ሆኖ እየተሰራበት እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ካሳቫ ሁለት ዓይነት ነው፡-ጣፋጭና መራራ ተብለው ይታወቃሉ። በኢትዮጵያ ስድስት ዝርያዎች የተለቀቁ ሲሆን ከነዚህ ዝርያዎች ውስጥ አምስቱ ዝርያዎች ከጣፋጭ ዝርያዎች እና ከምርታመነት አንፃር ዝቅተኛ ኬሌ ዝርያ 44/72 ሬድ 281ኩ/ል በሄ/ር እና ከፍተኛዉ መልኮ 108 ዝርያ 778 ኩ/ል የሚጠቀሱ ናቸዉ። የካሳቫ ሰብልን በስፋት ለማምረትና አርሶ/አርብቶ አደሮች ከምግብ ፍጆታ ባለፈ በኢኮኖሚው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የክልሉ ግብርና ቢሮ እየሰራበት ይገኛል። በክልሉ ኮንታና ዳውሮ ዞኖች ገቢያቸው እያደገ የመጡ ነዋሪዎች ብቅ ማለትም ጀምረዋል። የካሳቫ ሰብል ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሰራበትም ቢሮው በዘርፉ ላሉ ባለሙያዎች የአቅም ማጎልበቻ ግንዛቤ መፍጠር መቻሉንም እንዲሁ አቶ ተስፋዬ አብራርተዋል ።
የካሳቫ ሰብልን በስፋት ለማምረትና ዘር ለማዘጋጀት፡-ለዘር የሚውሉ ቁርጥራጮች አዘገጃጀት
ተቆርጦ ያልቆየ፣
ከተተከለ ቢያንስ 8 ወር የሞላው፣
ሲቆረጥ በስድስት ሰኮንዶች ውስጥ ፈሳሽ (ወተት) የሚያወጣ
ግንድ ከመካከለኛው ክፍል መሆን አለባቸው
ቁመቱ ከ20-30 ሳ.ሜ የሆነና ከአምስት ያላነሰ እንቡጥ እንዲኖረው ይመከራል ብለዋል።
የካሳቫ ሰብል ቆላማ እና ዕርጥበት አጠር አካባቢዎች በስፋት የሚመረት ነዉ። ለካሳቫ ሰብል አመራረት ሜዳማ የመሬት አቀማመጥ ምቹ ነው፡፡ ተዳፋትና ሸለቋማ የመሬት አቀማመጥ ያላቸው አካባቢዎች ለጎርፍና ለውሃ መተኛት የተጋለጡ ቢሆኑም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን አቀናጅቶ በመስራት ካሳቫን ማልማት ይቻላል ሲሉም አቶ ተስፋዬ ይገልጻሉ። ካሳቫ ጥሩ ምርት እንዲሰጥ መሬቱ ከ25-30 ሴ.ሜ በጥልቀት መቆፈርና መታረስ ያለበት ቢሆንም የማሳ ዝግጅት፡- በአየር ሁኔታ፣ በአፈር ዓይነት፣ በዕፅዋት ሽፋን፣ በመሬት ከፍታና ወዘተ የሚለያይ በመሆኑ ማሳው እንደ ሁኔታው በሚከተለው መልክ ሊዘጋጅ ይችላል፡፡ የደን መሬት ከሆነ በጣም አነስተኛ ወይም ምንም ዝግጅት አያስፈልገውም፤ ከባድ አፈር ወይም ውኃ የሚተኛበት ወይም ሸክላማ ከሆነ በጉብታ (Mound) ወይም በመደብ (ridge) ይዘጋጃል፤ አፈሩ ለስላሳና ቀላል ከሆነ ካሳቫ ለጥ ባለ መሬት ሊተከል ይችላል ።
የካሳቫ ሰብል በክልላችን እሰከ 9ሺ ሄ/ር እየተመረተ የሚገኝና ይህም በተለይ በኮንታና ዳዉሮ ዞን በስፋት የሚገኝ ሲሆን በሌሎች ዞኖች ጅምር ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝና ይህንንም በሁሉም ዞኖች lከ232 ሺህ በላይ የካሳቫ ሰብል ቁርጥራጮችን ለዘር ምንጭነት የሚዉል የማሰራጨትና ይህም ተግባር ተጠናክሮ እንዲተገበር እየተሰራበት እንደሚገኝ የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመላክታል።
