



በመኸር ግብርና እርሻ በዘር ከተሸፈነው ማሣ ውስጥ 37 ሄክታሩ የስንዴ ኩታ ገጠም እርሻ መሆኑን የወረዳው ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ጽ/ቤት ገልጿል።
እንደ ሀገር ትኩረት ከተሰጠባቸው የግብርና ዘርፎች ውስጥ አንዱ የስንዴ ልማት ነው።
ስንዴን ከምግብ ፍጆታ ባለፈ ወደ ውጭ እስከመላክ በመደረሱ ስራው ትኩረት እየተሰጠበት መጥቷል ።
በቤንች ሸኮ ዞን ሼይ ቤንች ወረዳ ስንዴን በክላስተር የማልማቱ ጉዳይ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በወረዳው የማሃ ቀበሌ አርሶአደሮች ከ20 ሄክታር በላይ መሬት ስንዴን በኩታ ገጠም እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከወረዳ ጀምሮ ቀበሌ ድረስ ያሉ ባለሙያዎች አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉላቸው አርሶአደሮቹ ገልፀዋል።
ወደ ስራው ከመግባታቸው በፊት ስልጠና መሠጠቱን ያወሱት አርሶአደሮች ዘርና የማዳበሪያ ግብአቶችን እንዳገኙም አመልክተዋል ።
አሁን ላይ የስንዴው አዝመራ በጥሩ ሁኔታ ለመገኘቱ ዋናው ምክንያት በጋራ ሆነው እርሻውን በመከታተላቸውና በመንከባከባቸው መሆኑንም ገልፀዋል።
የወረዳው ግብርና የአካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ጽ/ቤት የኤክስቴንሽን ኮሙንኬሽን በድን መሪ አቶ ሀብታሙ ሀይሌ በወረዳው በመኸር እርሻ 10ሺ 404 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን አመልክተው ከዚህ እርሻ 12 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚሰበሰብ ተናግረዋል ።
በወረዳው ማሃ እና ኩካ ቀበሌዎች 35 ሄክታር መሬት በስንዴ ኩታ ገጠም እየለማ ይገኛል ያሉት ቡድን መሪው ለእርሻ ስራው አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ተግባራት መከናወኑን አመልክተዋል።
ከስንዴ በተጨማሪ በቆሎ በኩታ ገጠም በስፋት እየተሰራበት መሆኑን አመልክተው የኩታ ገጠም እርሻ አርሶአደሩ ከአረም ቁጥጥር ጀምሮ በጋራ ማሣቸውን ለመንከባከብ ምቹ ሁኔታ ስለፈጠረላቸው በኩታ ገጠም የመስራቱ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን አመልክተዋ ሲል ቤንች ሸኮ ቴቪ ዘግቧል።
