ለግብርና መዋቅራዊ ሽግግር ስኬት የኅብረት ሥራ ማህበራት ቁልፍ ሚና…

Spread the love

ለግብርና መዋቅራዊ ሽግግር ስኬት የኅብረት ሥራ ማህበራት ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ አሉ የኢትዮጵያ የኅብረት ሥራ ማህበራት ኮሚሽነር አቶ ጌትነት ታደሰ፡፡

“ኅብረት ሥራ ለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የኅብረት ሥራ የልማት አመቻች ባለሙያዎች የስልጠና መድረክ በተለያዩ ከተሞች እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ኮሚሽነሩ በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የሲዳማ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኅብረት ስራ ማህበራት ባለሙያዎች የሥልጠና መድረክ ላይ እንዳሉት፥ ማህበራቱ ለግብርና መዋቅራዊ ሽግግር ስኬት ቁልፍ ሚና አላቸው፡፡

የኅብረት ስራ ማህበራት ተለዋዋጭ የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን በመረዳት ዘመናዊ አሰራርን በመከተል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ ያላትን ህልም ለማሳካት ማህበራቱ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመው፥ ይህንን ውጤት ማምጣት በሚያስችል አግባብ ሪፎርም ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት፡፡

እንደ ሀገር ከ89 ሺህ በላይ የኅብረት ሥራ ማህበራት በኮሚሽኑ ስር በ400 የገበሬዎች ኅብረት ስራ ማህበራት ዩኒየን እና በአምስት ፌደሬሽኖች ታቅፈው በስራ ላይ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

መድረኩ በተመሳሳይ በባህር ዳር ከተማ በመካሄድ ላይ ሲሆን፥ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከገበያ ማረጋጋት በላይ ለኢኮኖሚው ሁነኛ ሚና እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ በመድረኩ ላይ ተነስቷል፡፡

በጅማ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ተመሳሳይ መድረክ ከኦሮሚያ፣ ጋምቤላ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የተወጣጡ የኅብረት ስራ ማህበራት ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ ሲል ኤፍ ኤም ሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *