በቡና ምርት ጥራት፣ አቅርቦት እና በግብይት ስርዓቱ ላይ በትኩረት በመስራት ቡናን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየሰራ እንደሚገኝ የክልሉ ቡና ሻይ ቅመማ ቅመም ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

Spread the love

ባለስልጣኑ የታጠበ ቡና ምርት አዘገጃጀት እና ጥራት አጠባበቅ ላይ ከካፋ ዞን ለተውጣጡ የግብርና ባለሙያዎች እና ኢንዱስትሪ ባለቤቶች በቦንጋ ከተማ ስለጠና ሰጥቷል።

በስልጠናው በታጠበ ቡና ምርት ዝግጅትና ጥራት አጠባበቅ ፣ በቡና ግብይት አሰራር እንዲሁም የታጠበ ቡና ምርት አዘገጃጀት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቡና ሻይ ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ፣ የአካባቢውን ምቹ ምህዳር በመጠቀም የቡና ማሳ ሽፋን ከፍተኛ ቢሆንም በምርት ጥራት፣ አቅርቦት እና በግብይት ስርዓቱ ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።

ክልሉ በ2017 በጀት ዓመት 48 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ጠቁመው ካለው ሀብት አንጻር ለገበያ የሚቀርበው አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ከምርት ዝግጅት ፣ አቅርቦት እንዲሁም በገበያ ትስስር ላይ በጥንቃቄ በመስራት በመጠን እና በጥራት ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ ከዘርፋ የሚፈለገውን ጠቀሜታ ማግኘት እንዲቻል በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንዲወጡም አሳስበዋል።

በባለስልጣኑ የቡና ምርት ዝግጅት ባለሙያ የሆኑት አቶ ሽመልስ አራጋው እንዳሉት፣ስልጠናው በዘርፉ የተሰማሩ አካላት በእሼት ቡና አዘገጃጀት ላይ ያላቸውን ክፍተት ለመሙላት እና አቅም ለማሳደግ የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል።

ደረጃውን ያልጠበቀ መፈልፈያ ኢንዱስትሪ ፣ጥንቃቄ የጎደለው የቡና አደራረቅና አዘገጃጀት እንዲሁም በግብይት ማዕከላትና በተለያዩ ቦታዎች ጥንቃቄ የጎደለው አያያዝ ለቡና ጥራት ጉድለት ምክንያቶች እንደሆነም አብራርተዋል።

በባለስልጣኑ የግብይት ባለሙያና የምርት ዝግጅትና ገበያ ልማት ተወካይ አቶ መስፍን ሀ/ማርያም፣ የቡና ግብይት አሰራር ላይ ስልጠና በሰጡበት ወቅት እንዳሉት፣ በአሁኑ ጊዜ ተለዋጭ የሆነ ገበያ ሁኔታ ስላለ የግብይት ተዋናዮች የግብይት አሰራርን በመከተል ተወዳዳሪ እና ተፈላጊ ምርት ማቅረብ አለባቸው ብለዋል።

የኢንዱስትሪ ባለቤቶችም ሆኑ ሌሎች በቡና ግብይት ዘርፍ የተሰማሩ አካላት ለግብይት ማዕከላት የሚያቀርቡት የቡና ምርት ጥራቱ የተረጋገጠ እንዲሆን በጋራ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በካሳሁን አሰፋ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *