በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የባለድርሻ አካላት አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር መድረክ ተጀመረ

Spread the love

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ለባለድርሻ አካላት ያዘጋጀው አጀንዳ የማሰባሰብ እና ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተወካዮች መረጣ መድረክ ተጀምሯል።

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው በመድረኩ ባስተላለፉት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት የፖለቲካ፣ የማህበራዊ እና የኢኮኖሚ ችግር እንዳለባት ጠቁመው ይህንን ችግር በምክክርና በውይይት ፈተን ወደ ፊት ማራመድ አለብን ሲሉ ተደምጠዋል ።

የምክክር ሂደቱ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች በማሳተፍ ከወረዳ አንስቶ እስከ ሀገር ደረጀ በጥሩ ደረጀ እየተካሄደ እንደሚገኝ ኮሚሽነር ዘገየ ተናግረዋል፡፡

አጀንዳ የማሰባሰብ እና ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተወካዮች መረጣ መድረክ ላይ የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት በምክክሩ ወቅት በመደማመጥና በመከባበር እንዲሁም በሀሳብ የበላይነት መሆን እንዳለበት ኮሚሽነር ዘገዬ አሳስበዋል ።

ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በተለያዩ አካላት መካከል የሚስተዋለው ያለመደማመጥ፣ ያለመቻቻልና ያለመከባበር ለግጭት መፈጠር ምክንያት ሆኖ በሀገራችን እና በሌሎችም በርካታ ሀገራት ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።

በመሆኑም መሠረታዊ እና ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚታዩ የሀሳብ መለያየቶችንና አለመግባባቶች መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን አካታችና ሰፋፊ በሆኑ ሕዝባዊ መድረኮችን በማመቻቸት ምክክር በማድረግ ማግባባት ላይ መድረስ እና ተፈፃሚ እንዲሆን ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ ገልፀዋል ።

በምክክር ሂደቱ በሀገሪቱ ያለውን የፖለቲካ፣የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲቀረፉ ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅባቸውም ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ ጥሪ አቅርበዋል ።

የባለድርሻ አካላት አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር መድረክ ቀጥሎ በቡድን የሚደረግ ሲሆን በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ መድረክ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮች መረጣ የሚከናወን እንደሆነም ተገልጿል ።

ይህ ዛሬ የተጀመረው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የባለድርሻ አካላት አጀንዳ የማሰባሰብ እና ለሀገራዊ ምክክር ተወካዮች መረጣ የምክክር መድረክ ለተከታታይ ሦስት ቀናት እንደሚቆይ ተገልጿል።

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *