








በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ተሳትፏዊ ግብርና ለአየር ንብረት ሽግግር በእንግሊዝኛ ምህጻረ ቃል PACT ፕሮግራም ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በሚዛን ከተማ እየሰጠ ይገኛል።
ፕሮግራሙ በመጀመሪያው ምዕራፍ በክልሉ በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጉን የገለጹት በክልሉ ግብርና ቢሮ የተሳትፏዊ ግብርና ለአየር ንብረት ሽግግር ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ታመነ ተስፋዬ አሁን ላይ ወደ ትግበራ የገባው ፕሮግራሙ ለቀጣይ 7 ተከታይ አመታት ከ25 ሺህ በላይ ቤተሰብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
ፕሮግራሙ እንደሀገር ከተረጂነት ለመላቀቅ የተጀመረውን እንቅስቃሴ በጉልህ የሚደግፍ መሆኑን የገለጹት አቶ ታመነ በሁለት የክልሉ ዞኖች በተለዩ አምስት ወረዳዎች የግብርና ልማት ስራዎችን እንደሚደግፍ አብራርተዋል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው የባለድርሻ አካላትን ሀላፊነትና ተግባር በመለየት የፕሮግራሙን ተግባር በተሻለ እውቀት ለመምራት ያስችላል ያሉት የፕሮግራሙ አስተባባሪ ስልጠናው ከዚህም በተጨማሪ በባለድርሻ አካላት መካከል የጋራ ተግባቦትን የሚፈጥር እንደሆነም ጨምሮ ገልጸዋል።
በስልጠናው የፕሮግራሙ የክልልና የዞን የቴክኒክ ኮሚቴዎች እንዲሁም የወረዳ ስትሪንግ ኮሚቴ አባላት እየተሳተፉ የሚገኝ ሲሆን በፕሮግራሙ ዓለማና ዝርዝር ተግባራት ዙሪያ በኢፌዴሪ የግብርና ሚኒስትር የተሳትፏዊ ግብርና ለአየር ንብረት ሽግግር ፕሮግራም ከፍተኛ ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጡ ይገኛል።
በዕድገቱ በዛብህ
