ለቤንች ብሄር ዘመን መለወጫና ምስጋና በዓል (ቢስት ባር ) የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁ ተገለጸ።

Spread the love

ከግንቦት 29 እስከ ሰኔ 01 2016 ዓ ም በድምቀት ለሚከበረው የቤንች ብሄር ዘመን መለወጫና የምስጋና በዓል ቢስት ባር የቅድመ ዝግጅት ስራው መጠናቁን የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የበዓሉ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሀብታሙ ካፍትን ገለጹ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ በዓሉን ለማክበር በተሰሩ ስራዎች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

የቤንች ብሄር ዘመን መለወጫና ምስጋና በዓል ቢስት ባር ከዚህ ቀደም ሲከበር የነበረ ቢሆንም ለበርካታ አመታት የበዓሉ ሳይከበር ተቋርጦ መቆየቱን የገለጹት አቶ ሀብታሙ ካፍትን በዘንድሮው አመት በዓሉን በተደራጀ መንገድ ዳግም ለማክበር የዝግጅት ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በበዓሉ አከባበር ዙሪያ ከሀገር ሽማግሌዎች ከምሁራን ከአመራሩና ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደስራ መገባቱን ነው አቶ ሀብታሙ ካፍቲን የገለጹት።

በዓሉን ለማክበር የተቋቋመው ኮሚቴ በሰራው ስራ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ማሳተፍ መቻሉን የገለጹት አቶ ሀብታሙ ካፍትን በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ከአርሶ አደር እስከ ነጋዴ ከወጣት እስከ አዛውንቱ ሁሉም ያሳየው ተሳትፎ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

አጎራባች ዞኖች ያደረጉት ተሳፎም የሚያስደምም መሆኑን አንስተዋል።

የቢስት ባር በዓልን ለማክበር የታየው ተሳትፎ የአብሮነት መስተጋብር ጎልቶ የታየበት መሆኑን አስተዳዳሪው ጨምረው ገልጸዋል።

እስካሁን በተሰራው የሀብት ማሰባሰብ ስራ ከ16.7 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡ ተገልጿል።

በዓሉን በሚመለከት በነገው እለት የፓናል ውይይት የሚደረግ ሲሆን በቀን 29 የቤንች ብሄር መነሻ እንደሆነ በሚነገርለት ዣዥ ቀበሌ በዓሉ በይፋ የሚበሰር ይሆናል።

ሰኔ 01 በአማን የቀድሞ አየር ማረፊያ የበዓሉ ማጠቃለያ ፕሮግራም እንደሚደረግ ተገልጿል።

ህብረተሰቡ እስካሁን ያሳየውን ድጋፍ እስከ በዓሉ ፍጻሜ አጠናክሮ እንዲቀጥል የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን ጥሪ አቅርበዋል።

ለመላው የዞኑ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል ሲል የዘገበው ሚዛን አማን ፋና ኤም ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *