


ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ እና በጣሊያን-አፍሪካ ጉባኤ ላይ ብሔራዊ ጥቅሞቿን በሚያስጠብቁና ከፍ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ በንቃት ለመሳተፍ መዘጋጀቷን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፣ በአዲስ አበባ በሚካሄዱት ጉባኤዎች የሀገራት መሪዎች፣ ሚኒስትሮችና፣ ከፍተኛ ዲፕሎማቶችን ጨምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው እንግዶች ይታደማሉ።
ኢትዮጵያም ይህንን አጋጣሚ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበርና ተሰሚነቷን ከፍ ለማድረግ በንቃት እንደምትጠቀምበት ተጠቁሟል።
ከ17 ሺህ በላይ የልዑካን ቡድን አባላት በሚሳተፉባቸው ጉባኤዎቹን በብቃት በማስተናገድ አስፈላጊው ዝግጅት በመጠናቀቁ እንግዶችን መቀበል ተጀምሯል።
ኢትዮጵያ በኢነርጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በውኃ እና በመሠረተ ልማት ዘርፎች ያከናወናቸውን የለውጥ ሥራዎች ለሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞቿ የምታካፍልበትና አዳዲስ አጋርነቶችን የምትመሰርትበት ምቹ ቁመና ላይ እንደምትገኝ ተገልጿል።
በተለይም በምግብ ራስን መቻል፣ በኮሪደር ልማትና በአረንጓዴ ዐሻራ የተመዘገቡ ስኬቶች ለአህጉሪቱ በምሳሌነት እንደሚቀርቡ አቶ ተስፋሁን አንስተዋል።
ጉባኤውን ስኬታማ ለማድረግ 35 የፌዴራል ተቋማትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅንጅት ሲሠሩ መቆየታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ሆቴሎች፣ የትራንስፖርት አቅራቢዎችና የታክሲ አሽከርካሪዎች እንግዶችን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸው ተረጋግጧል።
የፀጥታና ደኅንነት ግብረ ኃይሉም በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል ታግዞ አስተማማኝ ጥበቃ እያደረገ ይገኛል።
መንግሥት በመግለጫው፤ አፍሪካውያን ወንድሞችና እህቶች ኢትዮጵያ በተፈተነችባቸው ወቅቶች ሁሉ ላሳዩት አጋርነት ምስጋና የምታቀርብበት መድረክ መሆኑን ተጠቁሟል።
የመዲናዋ ነዋሪዎችም እስከ ጉባኤው ፍጻሜ ድረስ ሊያጋጥሙ የሚችሉ መጠነኛ የመንገድ መስተጓጎሎችን በትዕግሥት እንዲያልፉና ለጉባኤው ስኬት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።
በቀጣይ ቀናት የአፍሪካ ዋና ዋና ጉዳዮች የሚወሰኑባትና የአህጉሪቱ “ዓይንና ጆሮ” የምትሆነው አዲስ አበባ፣ በአዳዲስ የመሠረተ ልማት ግንባታዎቿና በእንግዳ ተቀባይ ሕዝቧ አህጉራዊ ግዴታዋን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗ ተረጋግጧል።
ጉባኤውን ለመዘገብም የ800 ሚዲያ ባለሙያዎች የፈቃድ አሰጣጥ ሒደት በበይነ መረብ እንዲሳለጥ ተደርጓል ብለዋል።
