አዲሱ ትውልድ በዲጂታል ቴክኖሎጂ በአለም አቀፍ ደረጃ ብቁ ፣ ተወዳዳሪና ተፎካካሪ እንዲሆን መንግስት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፦ አቶ ግዛው ጋጊያብ

Spread the love

የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ በሚቀጥሉት 3 አመታት በክልሉ ከ140ሺ በላይ የኮደርስ ሰልጣኞችን ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚው ለመቀላቀል በሚዛን ማዕከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየሰጠ ነው።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛው ጋጊያብ የስልጠና መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ 2025 እስከ 2030 በአፍሪካ 5 በዲጂታል ቴክኖሎጂ ቀዳሚ ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።

በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ኢንሺዬቲቭ ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ጋር በመተባበር በሚቀጥሉት 3 አመታት 5 ሚሊየን የኢትዮጵያ ኮደሮችን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው እንደ ክልል 140ሺ ሰልጣኝ ኮታ መሰጠቱን ገልጸዋል።

ስልጠናው በዋናነት በቴክኖሎጂ ዘመን ውስጥ በአለም አቀፍ ደረጃ ብቁ ፣ ተወዳዳሪና ተፎካካሪ በመሆን በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ተጠቃሚ ለመሆን መሆኑን ገልጸዋል። ኮደርስ ህይወትን ይቀይራል ፣ ስራን ያቀላጥፋል ፣ ፈጠራን ያበረታታል ፣ የኑሮ ዘይቤን ከመቀየር ባሻገር በኢኮኖሚም ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

በአፍሪካ ኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ግዛው አዲሱ ትውልድ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎት እንዲኖራቸውና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው ብለዋል። በክልሉ በዚህ አመት ከ35ሺ በላይ ሰዎችን ለማሰልጠን ታቅዶ ወደ ስራ ውስጥ መገባቱን ገልጸው እስካሁን ከ15ሺ በላይ ሰዎች ስልጠናውን መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የአይሲቲና ኮምፒቲሺናል ሳይንስ ትምህርት ክፍል የሶፍትዌር ኢንጂነርንግ መምህር ይበልጣል አንዳርጌ ለኮደርስ ስልጠናዎችን እየሰጡ ይገኛሉ።

በክልሉ ሚዛን ማዕከል የሚገኙ የክልል ተቋማት ባለሙያዎችና አመራሮች ስልጠናውን እየወሰዱ ይገኛሉ ሲል የቤንች ሸኮ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *