በክልሉ የሚገኙ የመስኖ ተቋማት የግብርና ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የመስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በአመያ ከተማ አካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ የመስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ፋልታሞ ድብሎ በሀገሪቱ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ የተጀመረውን መፍጠር፣ መፍጠንና መዝለል መርህን በመከተል እየተሰራ ያለውን ስራ ለማስፈፀም እንደተቋም የተሰጡ ተልዕኮዎችን በተገቢው መፈፀም እንደሚገባ በመግለጽ ለዚህም ጥንካሬዎችንና ጉድለቶችን በመለየት መስራት ይገባናል ብለዋል።

በክልሉ የሚገኙ መስኖ ተቋማት በሚፈለገው ልክ በሙሉ አቅም እያለሙ እንደማይገኙ ያነሱት ኢ/ር ፋልታሙ የኢኮኖሚ ውጤታማነት እንዲመጣ ከባለድርሻ ተቋማት ጋር ቅንጅታዊ ስራዎችን በማጠናከር የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ መስራትና ለውጤታማነቱ ተግዳሮት የሚሆኑ ጉዳዮችን መቅረፍ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የኤጀንሲው ም/ዳይሬክተር ኢ/ር አፈወርቅ ዓለሙ የተቋሙ ተልዕኮ የክልሉ አርሶ አደሮችና ከፊል አርሶ አደሮች ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ ዘመናዊ የመስኖ ተቋማትን በመጠቀም ምርትና ምርታማነት ማሳደግና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መሆኑን በመግለጽ ተቋሙ ከራሱ ተግባራት ባሻገር ለሌሎች ተቋማት መሠረት መሆኑንም አስረድተዋል።

የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት የኤጀንሲው የልማት ዕቅድ ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ደስታ ተቋሙ በክልሉ በተለያዩ ዞኖች የመስኖ ተቋማትን በመገንባት ለህብረተሰቡ አገ/ሎት እንዲሰጡና ምርታማነት እንዲጨምር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀው በግማሽ ዓመቱ 470 ሄ/ር መሬት ማልማት የሚችሉ 7 የመስኖ ፕሮጀክቶች ጥናትና ዲዛይን ማከናወን መቻሉን ገልፀዋል።

ባለፈው ዓመት የተጀመሩ የጽልቤና ዳማ የመስኖ ተቋማት እንዲጠናቀቁ በማድረግ 93 የነበረውን የክልሉ የመስኖ ተቋማት ብዛት ወደ 95 ማድረስ መቻሉን የገለፁት አቶ ጌታቸው የተቋማትን ጥገናና ክትትል በማድረግ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች ለተቋሙ የተሰጠው ተልዕኮ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ፋይዳ ያለው ስለመሆኑ ጠቁመው ከዚህም አንፃር በበለጠ አቅም መስራት እንደሚጠበቅ አንስተዋል።

በተለይም የተገነቡ የመስኖ ተቋማት በሙሉ አቅም አገ/ሎት እንዲሰጡ መስራት፣ ፕሮጀክቶችን ለሚመለከታቸው ተቋማት በወቅቱ ማስተላለፍና ቅንጅታዊ ስራዎችን ማጠናከር እንዲሁም ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ መስራት ይገባል ያሉት ተሳታዎች የሚስተዋሉ ጉድለቶች በቀጣይ ዕቅድ ውስጥ በመከለስ በትኩረት መፈፀም ያሻል ብለዋል።

በክልሉ በአጠቃላይ 305,886 ሄ/ር መሬት በዘመናዊ መስኖ ሊለማ የሚችል መሬት እንደሚገኝም ተገልጿል ሲል የዘገበው የኮንታ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *