የተጀመረው ሀገራዊ ምክክሩ በሀገር ደረጃ ያሉ ችግሮችን በውይይትና በምክክር ለመፍታት ይጠቅማል፡- የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲና ማህበራት ተወካዮች

Spread the love

የተጀመረው ሀገራዊ ምክክሩ በሀገር ደረጃ ያሉ ችግሮችን በውይይትና በምክክር ለመፍታት የሚጠቅም መሆኑን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እየተካሄደ ባለው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ተሳታፊ የሆኑ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲና ማህበራት ተወካዮች ተናገሩ።

የደቡብ ምዕራብ ክልል ፖሊቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ ሀገራዊ ምክክሩ የሀሳብ የበላይነት ለማረጋገጥ የተፈጠሩ ችግሮችን በውይይትና በምክክር መፍታት ጠቃሚ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ለዚህም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እያከናወነ ያለው ተግባር ሀገርን የማገዝ ተግባር በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አቶ ሰለሞን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚበጀው ችግሮችን በጋራ በመሆን በውይይት መፍታት ወሳኝ የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትም የሁሉንም ፓርቲዎች የያዘ በመሆኑ በክልሉ የሚነሱ ማንኛውም ችግሮች በውይይት እና በምክክር ለመፍታት ከፍተኛ ድርሻ እንደለው የሚያምን መሆኑን አስተውቀዋል፡፡

መቶ አለቀ ተስፋዬ ናትናኤል ከቤንች ሸኮ ዞን የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ድጋፍ ማህበር ሰብሳቢ ናቸው፡፡ ምክክሩ ለሀገራዊ አንድነት የሚጠቅም መሆኑን አንስተው በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ መነጋገር ችግር የሚፈታ እንደሆነ ዕምነት እንዳለቸው አንስተዋል፡፡

የክልሉ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ቦርድ ሰብሳቢ ወታደር ጌታቸው ክፍሌ በበኩላቸው ምክክሩ በጣም ደስ የሚል እና ተስፋ ሰጪ መሆኑን አንስተዉ በአካል ጉዳተኞችን የሚመለከት አጀንዳዎች ለማስያዝ መድረኩ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጠሩ ችግሮች ሰለባ የሚሆኑ በአብዛኛው አካል ጉዳተኞች፣ ሴቶችና ህፃናት መሆናቸውን ጠቅሰው ግጭቶችን ለማቆምና በመወያየት ችግሮችን ለመፍታት ሀገራዊ ምክክር ቀጣይነት እንዲሆን አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ወ/ሮ ተናኝት ቶኮን ከሞቻ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ታሳታፊ ሲሆኑ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መምከር ከልጅነት ዕድሜ አንስተው ሲያስቡ እንደነበረ ጠቁመው በሀገራዊ አጀንዳ ላይ በመምከር የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አውስተዋል፡፡

በምክክር ላይ ለህዝብ ጠቃሚ ይሆናል የሚሉትን አጀንዳ ማዋጣታቸውንና በሂደቱ ለውጥ እንደሚመጣ መልካም ተስፋ መኖሩን ገልፀዋል፡፡

ጌሸራሻ አበጀ በሻ ከካፋ ዞን የማህበረሰብ ተወካይ ሲሆኑ ይህ ምክክር ለሀገሪቱና ለእኛም አዲስ ዕድልና ታርክ ነው ብለው ሀገር ብታሰባስብ መደማመጥ ቢኖር ብዙ ነገሮች የጎዳ ችግሮች እንደማይመጡ ተናግረዋል ፡፡

ለዚህም ይህ መሠረታዊ ነገሮች ታይቶ ከታች ጀምሮ ምክክር መደረጉን እጅግ ጠቃሚ እና ሀገር ወደፊት እንዲትቀጥል መልካም ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *