የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የአካባቢን ጸጋ መሰረት አድርጎ በመተግበሩ ውጤት እየተመዘገበ ነው::

Spread the love

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች የአካባቢን ጸጋ መሰረት በማድረግ ለሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በተከናወኑ ሥራዎች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑ ተገለጸ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የክልሎቹ የሥራ ሃላፊዎች እንደገለጹት መርሀ-ግብሩ የአካባቢን ፀጋ መሠረት ባደረገ መልኩ ተግባራዊ በመደረጉ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ ናቸው።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እንደገለጹት ሀገራዊው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርን ውጤታማ ለማድረግ የአካባቢን ፀጋ መሰረት ያደረጉ ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

“በክልሉ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የዶሮ፣ ወተትና ማር መንደር መመስረትን ያካተተ የማስተግበሪያ ስልት ተነድፎ እየተከናወነ ይገኛል” ብለዋል።

ለአብነት በዶሮ ልማት ሁሉንም የክልሉን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል አሰራር በመተግበር ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

አሰራሩ የዶሮ ልማቱን ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጀምሮ በሁሉም ቤተሰብ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በዚህም በክልሉ ከ500 በላይ የዶሮ መንደሮች የተፈጠሩ ሲሆን ባለፉት ዘጠኝ ወራትም 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአንድ ቀን እና የ45 ቀን ጫጩቶች ለማሰራጨት መቻሉን ተናግረዋል።

በወተት ልማት በኩል የላሞችን ዝርያ ማሻሻልና ጤና አጠባበቅና መኖ ልማት ሥራ ትኩረት እንደተሰጣቸው ገልጸው፣ በዚህም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ ሲሉ ተናግረዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፣ የሌማት ትሩፋትን ለማሳካት ያሉንን ጸጋዎች ታሳቢ በማድረግ እየሰራን ነው ብለዋል።

ማር እና እንስሳትን ጨምሮ በሌሎች የመርሀ-ግብሩ ትኩረቶች በተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ገልጸዋል።

ክልሉ ካለው የማር ምርት አቅም አንጻር በጥራትና በብዛት ለማምረት ባህላዊውን የንብ ቀፎ በሽግግርና በዘመናዊ ቀፎዎች የመቀየር ተግባር በትኩረት እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ከተጀመረ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ 222 የማር መንደሮች ተፈጥረዋል ያሉት አቶ ማስረሻ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ከ40ሺህ በላይ ዘመናዊ የሽግግር ቀፎዎች መሰራጨታቸውን ገልፀዋል።

በበጀት ዓመቱ በክልሉ ከ69 ሺህ ቶን በላይ ማር ለማምረት መታቀዱንና ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ32 ሺህ ቶን በላይ ማር ተመርቶ ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በሥጋ ምርት ልቆ ለመውጣት የአካባቢውን ጸጋ ላይ ያተኮረ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በዚህም አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

በተለይ በልዩ የሥጋ ጣዕሙና በመሞከት የሚታወቀውን የቦንጋ በግ በስፋት ተደራሽ ለማድረግ በተደረገ እንቅስቃሴ ከ20 ሺህ በላይ እናት እና 6 ሺህ ኮርማ በጎች መሰራጨታቸውን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *