አቶ አደም ፋራህ በአዳማ ከተማ አስተዳደር የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ጎበኙ

Spread the love

በምክትል ጠቅላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በአዳማ ከተማ አስተዳደር የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ጎበኙ።

አቶ አደም ፋራህ፣ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በአዳማ ከተማ አስተዳደር በሁሉም የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በተናበበና በተቀናጀ መልኩ በአንድ ማዕከል ለመስጠት የተቋቋመውና “ጋዲሳ ኦዳ” የሚል ስያሜ የተሰጠውን የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ነው በዛሬው ዕለት የጎበኙት።

ጉብኝቱን አስመልክቶ በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክትም፣ 29 ሴክተሮችን በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ በቴክኖሎጂ በተደገፈ አግባብ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለው ስርዓት የባለጉዳዮችን እንግልት የቀነሰ፣ ገቢን ለመሰብሰብ ምቹ የሆነ፣ ልማዳዊ የሆነውን የወረቀት ሥርዓት ከ80 በመቶ በላይ በሁሉም ሴክተሮች ውስጥ ያስቀረ መሆኑን ገልጸዋል።

አክለውም የአሰራር ግልፅነት እና ተጠያቂነትን ለማስፈን እና ሌብነትንና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ከፍተኛ እድል የፈጠረ መሆኑን አይተናል ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በከተማ ደረጃ ያሉ ተቋማትን በአንድ ማዕከል ከማሰባሰብ ባሻገር፣ የክፍለ ከተማ እና የወረዳ ተቋማትም በአንድ ማዕከል እንዲሰሩ ማድረጉ እጅግ የሚበረታታ እና ለሌሎች ከተማ አስተዳደሮችም ተሞክሮ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በከተማ አስተዳደሩ በኩል ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች መሬትን ሙሉ ለሙሉ በካድስተር ቴክኖሎጂ ዲጅታል ለማድረግ የተሄደበት ርቀት፣ በከተማዋ የሚኖሩ ዜጎች ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል የተዘረጋው የሲሲቲቪ ካሜራ ዝርጋታ ውጤታማ ነው ብለዋል።

በዚህም በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በምርጥ ተሞክሮነት ተወስዶ ተግባራዊ እንዲደረግ እንደ ብልፅግና ፓርቲ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በቀጣይ የሚሰራበት መሆኑን ነው ያስታወቁት።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *