ኢትዮጵያ የፊታችን ሰኞ ብሪክስን በይፋ በአባልነት ትቀላቀላለች

Spread the love

ኢትዮጵያ የፊታችን ሰኞ ብሪክስን በይፋ በአባልነት ትቀላቀላለች

በነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ 15ኛው የብሪክስ አባል አገራት ጉባኤ መካሄዱ ይታወቃል።

በነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ በተካሄደው 15ኛው የብሪክስ አባል አገራት ጉባኤ ኢትዮጵያ የአምስት አገራት ጥምረት የሆነውን ማህበር ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ የሚታወስ ነው።

ጥምረቱ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ግብጽ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ሳዑዲ አረቢያና ኢራን እ.ኤ.አ ከ ጥር 1 ቀን 2024 ጀምሮ በይፋ የብሪክስ አባል እንደሚሆኑ አስታውቋል።

አምስቱ አገራት ጥምረቱን ሲቀላቀሉ የአባል አገራቱ ቁጥር ወደ 10 ከፍ ይላል።

ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ለኢትዮጵያ ታላቅ ሁነትና መልካም አጋጣሚ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በወቅቱ መግለጻቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመልዕክታቸው ኢትዮጵያ ሁሉን አካታች ለሆነና ለበለፀገ የዓለም ስርዓት መስፈን ከሁሉም ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል ለባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ማደግና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሚናው የላቀ መሆኑን ምሁራን ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ በዓለም የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ተሰሚነቷና ተቀባይነቷ እንዲያድግ ብሪክስን መቀላቀሏ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለውም በመጠቆም።

ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጥረቷን በማጠናከር በተለይም በአህጉራዊ መድረኮች አፍሪካን በመወከል የመሪነት ሚናዋን በአግባቡ ለመወጣትና ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ጥምረቱን መቀላቀሏ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥርላት መሆኑንም አንስተዋል።

የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታት ብሪክስ ሌላ አማራጭ መሆኑንና ለንግድና ኢንቨስትመንት መሳለጥም ወሳኝ መሆኑ ታምኖበታል።

የብሪክስ አገራት ጥምረት እውን የሆነው እ.አ.አ 2006 ላይ በኒውዮርክ ከተማ ሲሆን፤ በወቅቱ ሲካሄድ ከነበረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ ጎን ለጎን የብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ያካሄዱትን ስብሰባ ተከትሎ ነው፡፡

እ.አ.አ 2011 በተካሄደው የጥምረቱ ሶስተኛው ጉባኤ ላይ ደቡብ አፍሪካ አባል ሆና አምስት አባላት ወዳሉት ጥምረት የተሸጋገረ ሲሆን፤ ይህንን ተከትሎ የጥምረቱ ስያሜም የአገራቱን መጠሪያ የመጀመሪያ ፊደላት በመያዝ ወደ BRICS ተለውጧል።

የብሪክስ ጥምረት ዓላማ የጋራ የሆኑ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ማረጋገጥ ነው፡፡

በዚህም የዓለምን ኢኮኖሚያዊና ፋይናንሳዊ አሰራሮችንና ንድፎችን ማሻሻል እንዲሁም የዓለም አቀፍ ሕግ መርሆዎችንና መመዘኛዎችን ማጠናከርና የተለያዩ ዘርፎችን ተደጋጋፊነት ማጠናከርን ያካትታል።

የብሪክስ አባል አገራት በዓለም አቀፍ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ፋይናንስ ስርዓትና አስተዳደር ላይ ያላቸው ትብብር እያደገ በመሄድ ላይ ነው፡፡

የጥምረቱ አባል አገራት ከዓለማችን ህዝብ 40 በመቶ የሚገኝባቸው፣ 26 በመቶ የዓለምን የምርት ምጣኔ የሚሸፍኑ እና 50 በመቶ የሚጠጋ የዓለም ኢኮኖሚ እድገት ባለቤቶች ናቸው።

ጥምረቱ አዲስ አባል አገራቱን መጨመሩ በዓለም የዲፕሎማሲ፣ ንግድና ኢኮኖሚ ዘርፍ ያለውን ተጽእኖ እንደሚያሳድግለት ተንታኞች ይገልጻሉ።

በጆሃንስበርጉ ጉባኤ አርጀንቲና ያቀረበችው የአባልነት ጥያቄ ተቀባይነት ያገኘ ቢሆንም ከአንድ ወር በፊት የአገሪቷ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት ጃቪየር ሜሌ ከሳቸው በፊት የነበሩትን ፕሬዝዳንት አልቤርቶ ፈርናንዴዝ የአባልነት ጥያቄ በመሻራቸው ብሪክስን እንደማትቀላቀል ተገልጿል።

(ኢዜአ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *