


በካፋ ዞን የንብ ልማት ከተደራጁ ኢንተርፕራይዞች መካከል አንዱ የሆነዉ ሜሊፌራ ካፋ ንብ ልማት ኢንተርፕራይዝ በማር ምርት ዉጤታማ መሆናቸዉን ተናግሯል።
የማር ምርትና ምርታማነትን ጥራት በጠበቀ መልኩ ለማሳደግ እየሰራን ነዉ በማለት ሚሊፌራ ካፋ ንብ ልማት ኢንተርፕራይዝ ሰብሳቢ አቶ ፋሲካ ኃ/ማርያም ተናግሯል።
በአለማችን ከሚሰሩ ስራዎች ዉስጥ ከፍተኛ እዉቀት የሚጠይቅ ስራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ፋሲካ በትንሽ ቦታ ብዙ ወጪ ሳይጠይቅ የተሻለ ዉጤት ማምጣት የሚያስችል የስራ ዘርፍ እንደሆነ ገልጿል።
የማር ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ሀገር በቀል ዛፎችንና የተለያዩ ማዓዛ ያላቸዉ አበባዎችን በዙርያ መትከልና ማስዋብ እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።
ሜሊፌራ ካፋ ንብ ልማት ኢንተርፕራይዞች በጥራት የማር ምርት በማዘጋጀት ዉጤታማ መሆናቸዉን በመግለጽ ሰም፣የማር ሙጫ እና ሌሎች ከማር ጋር ተያያዥ ያላቸዉን ምርቶችን በቀጣይ በማምረት ለገበያ እናቀርባለን ብሏል።
ሜሊፌራ ካፋ ንብ ልማት ኢንተርፕራይዞች የሳይት ባለሙያ አቶ ወንድማገኝ ታደሰ እንዳሉት የማር ምርት በካፋ ዞን ከቡና ቀጥሎ የሚታወቅና የሚመረት ምርት እና ለረጅም አመታት መቆየት የሚችል፣ ለምግብነትና ለመድሐኒትነት የሚጠቀም ምርት ነዉ ብለዋል።
ሜሊፌራ ካፋ ንብ ልማት ኢንተርፕራይዞች በ2006 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ንብ ማነብ ስራ የገባ ሲሆን በቋሚነትና በጊዜያዊነት ለ8 ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠራቸዉን ገልጸዋል ሲል የካፋ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።
