የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ለቱሪዝም ዘርፉ መዳረሻዎችን ብቻ ሳይሆን መሰረተ ልማቶችንም አበርክተዋል :-አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ

Spread the love

የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ለቱሪዝም ዘርፉ መዳረሻዎችን ብቻ ሳይሆን መሰረተልማቶችን በማበርከት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኙ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገለጹ።

የገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆነው ጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከትናንት በስቲያ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ጨበራ ዝሆን ዳና ሎጅ በገበታ ለሀገር ከለሙት መዳረሻዎች መካከል መሆኑን ጠቅሰው ፕሮጀክቶቹ ለቱሪዝም ዘርፉ ከመዳረሻነት ባሻገር መሰረተልማቶችን በማሟላት ትልቅ ሚና እያበረከቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚገኘውን ጨበራ ጩርጩራ ፓርክን እንደ ምሳሌ ያነሱት አምባሳደር ናሲሴ ፓርኩ በርካታ የተፈጥሮ ጸጋዎችን ቢላበስም ከመሰረተልማት አለመኖር አኳያ በተፈለገው መጠን ያለመጎብኘቱን አስታውሰዋል።

በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በተሰራው የመሰረተልማት ስራ ግን ፓርኩ ያለው እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለሚመጡ ጎብኚዎች ተደራሽ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ነው ያሉት።

በዚህም ጨበራ ዝሆን ዳና ሎጅ ተፈጥሮን ሳይጋፋ፣ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ፣ ውበት ባለውና መልከአምድሩን ማድነቅ በሚያስችል መልኩ ምቹና ዘመናዊ ማረፊያ ስፍራ ተገንብቶ ለቱሪስቶች ቀርቧል ብለዋል።

ይህም በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ተፈጥሮን ሳንጋፋ፣ እየተንከባከብንና የፈተጥሮ ውበትን የሚያጎሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማልማት ልምምዳችን ከፍ እያለ መምጣቱን ማሳያ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በቀጣይ በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ሰፊ የሚባሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች በመላው ሀገሪቱ በመገንባት ላይ ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ እነዚህም የኢትዮጵያን ገጽታ ከማስተዋወቅ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *