




የብልህ ጅምር(RISE) በወጣቶችና አፍላ ወጣቶች የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት አፈጻጸም ግምገማ ተደርጓል።
የብልህ ጅማሮ (RISE) ከ15_19 የዕድሜ ክልል ውስጥ ሆነው ያሉ ያገቡ የወጣቶችና የአፍላ ሴት ወጣቶችን ስነ ልቦና፣ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በክልሉ ፕሮግራሙ በተመረጡ ወረዳዎች ሲሰራ ቆይቷል።
በዚህ የፕሮግራሙ የአፈጻጸም ግምገማ ላይ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በክልሉ የእርግዝና ምርመራ ከተደረገባቸው እናቶች ውስጥ 17 % የሚሆኑት አፍላ ወጣቶች መሆናቸውን ተናግረዋል ።
ዕድሜያቸው ከ15_19 በሆኗቸው አፍላ ወጣቶች ያገቡትን በመለየት የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ፕሮግራሙ እውን ከተደረገ 8 ወራት ጊዜ ጀምሮ የተሻሉ ስራዎች መከናወናቸውን አቶ ኢብራሂም ተናግረዋል ።
በክልሉ ሁሉም ዞኖች የአፍላ ወጣቶች እርግዝና መኖሩን ያመላከቱት አቶ ኢብራሂም ይህም በስፋት የሚስተዋለው ካፋና ዳውሮ ዞኖች በመሆኑ ልዩ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚገባም አቶ ኢብራሂም አብራርተዋል ።
በፕሮግራሙ አተገባበር የሚስተዋለውን የመረጃ ጥራትና የአፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን አመራሩና የጤናው ባለሙያ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸውም አመላክተዋል ።
በዚህም የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሞችን በተገቢው ተግባራዊ በማድረግ በቀጣይ ጊዜያት በብልህ ጅምር RISE አፍላ ወጣቶች የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት ሊሰራበት ይገባልም ብለዋል።
በብልህ ጅምር አፈጻጸም በክልሉ ፕሮግራሙ ከያዛቸው 20 ወረዳዎች ውስጥ 3 ወረዳዎች የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው ሲሆኑ ቀሪዎቹ ካስመዘገቡት መካከለኛና ዝቅተኛ አፈጻጸም ፈጥነው መውጣት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አቶ ኢብራሂም ተናግረዋል ።
ዕድሜያቸው ከ15_19 የሆናቸው ያገቡ ወጣቶች የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተዘረጋው አሰራር መሠረት ወጣቶችን ወደተሻ ደረጃ በስነ ልቦና ፣በኢኮኖሚ እና መሰል ጉዳዮች አመራሩና ባለሙያው በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል ።
በኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ተወካይ ወ/ሮ ፋንታነሽ ደሳለኝ በበኩላቸው የጤና አገልግሎት ስራዎች ተደራሽነትን ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ስኬታማነት እንደ ሀገር ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሰጡበት እንደሚገባም ጠይቀዋል።
ጥራት ላለው የቤተሰብ ዕቅድ ተደራሽነትም ሁሉም ኃላፊነቱን በተገቢው ሊወጣ እንደሚገባውም ወ/ሮ ፋንታነሽ ደሳለኝ ገልጸዋል።
ክልላዊ የብልህ ጅምር (RISE) የ8 ወራት አፈጻጸም ሪፖርት፣ በዓለም ለ17ኛ ጊዜ፣ በሀገር አቀፍ ለ9ኛ ጊዜና በክልል አንደኛው የቤተሰብ ዕቅድ ቀን አከባበር ፣የISM የፕሮግራም አፈጻጸሞች ቀርበው የተገመገመ ሲሆን ተሳታፊዎች አስተያየት እና ጥያቄዎችን አንስተዋል።
በግምገማው ላይ የክልሉ ጤና ቢሮ አመራሮች ፣የዞንና የወረዳ የጤና ባለሙያዎች ፣ አጋር ድርጅቶችና የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር ተወካዮችና የወጣቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።
በታጠቅ አበበ
