ኢትዮጵያ እና ማሌዢያ ከዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ባሻገር

Spread the love

ኢትዮጵያ በደቡብ ምስራቅ እስያ ከምትገኘውና የቅይጥ ኢኮኖሚ ባለቤት ከሆነችው ማሌዢያ ጋር ዲፕሎማሲያ ግንኙነቷን የጀመረችው በአውሮፓውያኑ 2003 ነው።

በዚሁ አመት ኢትዮጵያ በሀገሪቱ ዋና ከተማ ኳላላምፑር ቆንፅላ ጽሕፈት ቤቷን በመክፈት የሁለትዮሽ ግንኙነቱን በዲፕሎማሲ አጠናክረዋለች።

ቆንፅላ ጽሕፈት ቤቱም በሀገራቱ መካከል ያለውን የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማሳደግ ስራዎችን በመስራቱ ብዙ የማሌዢያ ኩባንያዎች በእርሻና በማዕድን ዘርፍ ተሰማርተው ይገኛሉ።

ማሌዢያ ቅይጥ ኢኮኖሚ ያላት ሲሆን በተለይም ኤሌክትሮኒክስ፣ ፔትሮሊየም እና የተፈጥሮ ጋዝ ወደውጭ በመላክ ትታወቃለች።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ከሩስያ የብሪክስ ጉባዔ በኋላ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማሌዢያ ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ኳላላምፑር አየርማረፊያ ሲደርሱም በከፍተኛ ደረጃ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከማሌዢያ አቻቸው ጋር በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በዘላቂ ልማት፣ በጤና፣ በቱሪዝም እና በትምህርት ትብብር ላይ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ በተጨማሪም የሁለቱ ሀገራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የጋራ ጉዳዮች ላይም ይመክራሉ።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ይፋዊ ጉብኝት በማሌዢያ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት የበለጠ ይጨምራል።

ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 2023 በአፍሪካ አህጉር የማሌዥያ 26ኛዋ ትልቅ የንግድ አጋርም ነች።

በአውሮፓውያኑ 2005 የኢትዮጵያ ማዕድን ሚኒስቴር የማሌዢያ የነዳጅ ኩባንያ ጋር የአራት ዓመታት የነዳጅ ፍለጋ እና ምርት ስምምነት ተፈራርሟል።

ሌላ የማሌዢያ ኩባንያ በ285 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት በሻላ ሀይቅ አቅራቢያ 60 ሄክታር የሚሸፍን የእንጉዳይ እርሻን አቋቁሞ በመስራት ላይ ይገኛል።

ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱም ሀገራት በአየር ትራንስፖርት ላይ እየሰሩ ሲሆን የማሌዢያ አየር መንገድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የኮድሼር ስምምነትንም አለው ሲል የዘገበው የማሌዢያ ዜና ወኪል በርናማ ነው ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *