



ለመልካም አስተዳደር ጥያቄዎቻችንን መንግስት ምላሽ እየሰጠ ያለበት ሁኔታ የሚያስደስት ነው ሲሉ የያዶታ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በካፋ ዞን ሳይለም ወረዳ መንግስት ለዘመናት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆነው የሰነበቱ የልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ምላሽ እየሰጠ መምጣቱ ይበልጥ የህብረተሰቡን ተነሳሽነት እያሳደገ መምጣቱን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ ከወረዳው አስተዳደር ጋር በመተባበር በራስ አቅም የተለያዩ የልማት ስራዎችን ማከናወን መቻላቸውን ተናግረዋል ።
መንግስት በከተማው ከዚህ ቀደም ግንባታቸው ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ለይቶ አፋጣኝ ምላሽ እየሰጠ መምጣቱ ይበልጥ በልማት ላይ ተሳተፏችን እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል።
የያዶታ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትያል ኮሌጅ ለዓመታት ግንባታው ተቋርጦ መቆየቱ የአካባቢው ወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ መቆየቱን ተናግረዋል ።
አሁን ላይ ኮሌጁ መመረቁ የአካባቢው ወጣቶች የአካባቢውን ጸጋ ወደ ተሻለ ውጤት ለመቀየር ያለው ፋይዳ ይጎላል ሲሉም ተናግረዋል ።
በርካታ ወጣቶች ወደ ሌላ አካባቢ በመሄድ ይቸገሩ የነበረውን በእጅጉ በመቅረፍ ተወዳዳሪና በክህሎት የዳበረ ትውልድ ለመፍጠርም ያግዛል ብለዋል።
በሌላ በኩልም በጤናው ዘርፍ ወረዳው እያስመዘገበ ያለው ውጤት የሚደነቅ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ የክልሉ መንግስት የህብረተሰቡን ችግር በመረዳት አነስተኛ ቀዶ ጥገና ማዕከል በከተማው ጤና ጣቢያ እንዲጀመር መደረጉ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል ።
በተመረቁ ተቋማት የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉም እንደወትሮው ሁሉ የሚጠበቅብንን ድርሻ እንወጣለን ሲሉም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል ።
በታጠቅ አበበ
