




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከፍተኛ መጠን ያለውን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ከግምባር ቀደሞቹ ተርታ የሚመደብ ቡና አምራች አከባቢ ነው።
በክልሉ ቤንች ሸኮ ዞን፣ ደቡብ ቤንች ወረዳ ቡና በስፋት እንደሚለማ የገለጹት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተሾመ ኪያስካ በዚህም የአምራች አርሶአደሮች ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።
የቡና ጥራት ለማስጠበቅ ተግባራዊ የኾነው የቡና ፓኬጅ ማሻሻያ ውጤት ማምጣቱን የጠቆሙት አቶ ተሾመ በዚህም የጥራት ደረጃውን የጠበቀ እሸት ቡና ለኢንዱስትሪዎች እየቀረበ ይገኛል ብለዋል።
የቡና ፓኬጅ ማሻሻያ የቡና ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር ስፔሻሊት ቡናን በማዘጋጀት አርሶአደሩ ተጠቃሚ እንዲኾን እንዳስቻለውም አስረድተዋል።
የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ የእርሻና ኅብረት ሥራ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዩሐንስ ደጀኔ በበኩላቸው፥ በወረዳው ከ35ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በቡና መሸፈኑን ገልጸው፣
በወረዳው በእሸት ቡና ምርት ዝግጅት ከተሰማሩት 42 ኢንደስትሪዎች በዘንድሮ በጀት ዓመት እስካሁን 7ሺህ ቶን ማቅረብ መቻሉን አስረድተዋል።
ዘርፉ ለበርካቶች የሥራ ዕድል የፈጠረ እንደኾነ የጠቆሙት ኃላፊው በወረዳው 4 አልሚ አርሶአደሮች እና 6 የግል ባለሀብቶች በቡና ልማት ዘርፍ ተሰማርተው ይገኛል ብለዋል።
በወረዳው በእሸት ቡና ዝግጅት ሥራ የተሰማራው የአደራ ሰይድ ኢንዱስትሪ ስራ-አስኪያጅ አቶ አሰራር አሕመድ እንደገለጹት ድርጅቱ ከ3ሺህ ቶን በላይ የታጠበ ደረጃ አንድ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ይገኛል ብለዋል።
የቡና ምርትና የጥራት ደረጃው ካለፉት ዓመታት ጋር ስነጻጸር የተሻለ እንደኾነ ያመለከቱት አቶ አሰራር፥ በዚህም ከዕቅዱ በላይ ለማሳካት የሚያስችል ዝግጅት መኖሩን ጠቁመዋል።
የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ዜጎች በበኩላቸው፥ ከኢንዱስትሪው ተጠቃሚ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
