



ኢትዮጵያ በብራዚሏ ከተማ ቤሌም እየተካሄደ ባለው 30ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓመታዊ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ30) እየተሳተፈች ነው፡፡
ኮፕ30 ጉባዔ በብራዚል ቤሌም በይፋ የተጀመረ ሲሆን ጉባዔው በቀዳሚነት የዓለም የሙቀት መጠንን ወደ 1.5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ላይ እንደሚያተኩር ተገልጿል።
በፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ፣ ከጉባኤው ጎን ለጎን በሁለትዮሽ እና በባለለብዙ ወገን ውይይቶች ላይ እንደሚሳተፍ ተጠቁሟል፡፡
በጉባኤው በኢትዮጵያ ፓቪሊዮን እና ሌሎች ቁልፍ ቦታዎች ላይ ማሳያዎች እና የተለያዩ ክንውኖች እንደሚካሄዱም ተጠቅሷል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም አረንጓዴ ዐሻራን ጨምሮ እየወሰደቻቸው ያሉ ተግባራዊ እርምጃዎችን በጉባዔው አጉልታ በማሳየት ልምዷን እንደምታካፍል ተመላክቷል፡፡
በሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ (ACS2) የተነሱ የኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ እና ሌሎች ለአየር ንብረት ተጋላጭ የሆኑ ሀገራት ጉዳዮች እና ጥቅሞች እንዲጠበቁ ኢትዮጵያ በጉባዔው ሀሳቧን እንደምታንጸባርቅ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
በብራዚል እአአ ከኅዳር 10 እስከ 21 በሚካሄደው 30ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ፤ የአየር ንብረት ለውጥን እንዴት መቋቋም እንደሚቻል ለመወያየት የሀገራት መሪዎችን፣ ሚኒስትሮችን እንዲሁም ተደራዳሪዎች እና የተለያዩ ተወካዮች ተሰባስበዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
