
የትራንስፖርት አገልግሎት ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች እንዲሳለጡ ከፍተኛ ሚና ከሚጫወቱ ዘርፎች አንዱና ዋነኛው መሆኑን በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ማረጋገጥ እንችላለን።
የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ዘርፍ በአስፈላጊነቱ ልክ በተዋንያኖቹ ምክንያት በሚፈጠሩ ህገ ወጥ አሰራሮች በዜጎች ላይ የኑሮ ጫና ከመፍጠሩም በላይ ለመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችም ሰፊውን ድርሻ እንደሚወስድ አጠያያቂ አይደለም።
ከቅርብ ጊዜ ወድህ በዓለም አቀፍ ገበያ ጫና የነዳጅ እና መለዋወጫ እቃዎች ዋጋ መጨመርን እንደ ምክንያት በመውሰድ በዜጎች ላይ አላስፈላጊና የተጋነነ ታሪፍ ጭማሪ ማድረግ፤ ከተሽከርካሪ አቅም በላይ በመጫን እንዲሁም የትራንስፖርት ህጎችን ባለማክበር የሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ለመዳሰስ ከክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ምክትል ኃላፊና የትራንስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዘመዴ አንዳርጌ ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ!
መ/ኮ: ለቃለመጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍላችን ስም አመሰግናለሁ!
አቶ ዘመዴ አንዳርጌ: እኔም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥታችሁ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ!
መ/ኮ: የትራንስፖርት ዘርፉን ተገልጋዩ በሚፈልገው ደረጃ ለማዘመንና ለማሻሻል ምን እየሠራችሁ ነው?
አቶ ዘመዴ አንዳርጌ: እንደሚታወቀው የትራንስፖርት ዘርፍ የማያንኳካው ደጅ የለም ማለት ይቻላል። ሰዎች ይንቀሳቀሱበታል፣ ለፍጆታቸው የሚሆን የሸቀጣሸቀጦች ይዘዋወሩበታል፣ ሌሎች ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ይከናወንበታል። የትራንስፖርት ዘርፉ ሲዛባ የሰው ልጅ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችም ይንገጫገጫሉ።
ስለዚህ የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ ማዘመን አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ይኸን ስንል ደግሞ በዘርፉ ላይ የሚስተዋለው የአስራር ክፍተቶችና ተግዳሮቶች ቀድመው መታረም አለባቸው ብለን እየተንቀሳቀስን ነው።
መ/ኮ: በእርግጥ እንቅስቀሴዎች ይኖራሉ፣ ነገር ግን በየጊዜ በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ አቤቱታዎችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ምን የተለየ እርምጃ ትወስዳላችሁ?
አቶ ዘመዴ አንዳርጌ: ችግሩ በአንድ ተቋም ብቻ የሚፈታ ስላልሆነ በክልሉ ካሉ የተለያዩ ተቋማት ጋር ተቀናጅተን እና አስተባብረን እየሰራን ነው። ከዋና ዋና ተቋማት መካከል የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ፣ ጤና ቢሮ እና ትምህርት ቢሮ ይገኙበታል።
ከእነዝህ ተቋማት የህግ ማስከበሩን እና የቁጥጥር ስራዎችን የፖሊስ መዋቅር የሚሰራ ሲሆን መስመር ላይ ከሚሰጡት የግንዛቤ ማስጨበጫ አስከ ህግ ማስከበር ስራ ድረስ ከትራንስፖርት ዘርፍ መንገድ ተቆጣጣሪዎች ጋር በመሆን ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።
ይህ ስራ በየጊዜ ድጋፍና ክትትል ስለሚያስፈልግ ከላይ ከተጠቀሱት ተቋማት የተወጣጡ ግብረ ኃይሎችና ስትሪንግ ኮሚቴዎች በየደረጃ ባሉት መዋቅሮች ጋር አገልግሎት እየሰጡ ነው።
የመንገድ ደህንነትና ትራፊክ ቁጥጥር ግብረ ኃይል በውስጡ የቴክኒክ ኮሚቴ አዋቅረው አጣቃላይ የቁጥጥር ስራ እና ቅድመ አደጋ መከላከል ስራ እየሰሩ የትራፊክ ግጭት ሲከሰትም ፈጣኝ ምላሽና ማጣሪያ ያደርጋሉ።
መ/ኮ: ከላይ የተጠቀሱ አሠራሮች መኖራቸው አውን ቢሆንም ራሱ የቅሪታ ምንጭ እንዳይሆን ምን እየተደረገ ነው?
አቶ ዘመዴ አንዳርጌ: እነዝህ ጉዳዮች በቅርበትና በየሩብ ዓመቱ ተከታትለን እየገመገምን እናርማለን። በዚህም የቢሮው ኃላፊና ፖሊስ ኮሚሽር በተገኙበት ክልላዊ ንቅናቄ ተደርገው እስከ ወረዳ ባሉት መዋቅሮች የባለድርሻ ውይይትና የዘርፉ ግምገማ እንዲደረግ ተግባብተን ብዙ የማጥራትና የማስተካከል ስራ እየተሰራ ነው።
ይኸንን ግምገማ መሠረት በማድረግ ሠራተኞችን የማሸጋሸግ፣ በስልጠና የማብቃትና ሌሎች እርማጃዎች እየተወሰዱ ሲሆን በፖሊስ በኩል ደግሞ የትራፊክ ፍሰት ላይ የሚሰሩት ፖሊሶች ዙሪያ ሪፎርሞች ተጠናክሮ ቀጥለዋል።
አሠራሩን ለመዘርጋት በቅድሚያ ተቋማዊ ሪፎርሞችን ከውስጥ መጀመር አስፈላጊ ነው። የአገልግሎት አሰጣጥ ብቃትና ስነ ምግባርን መሠረት አድርገን እየሰራን ሲሆን የፖሊስ መዋቅሩም በራሱ ይኸን ተግባር እየከወነ መሆኑ እንቅስቃሴያችንን የተሰናሰለ ያደርገዋል።
መ/ኮ: ስለ ትራንስፖርት ዘርፍ ሲናነሳ የመናኸሪያዎች አገልግሎት አሰጣጥ ጉዳይ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳልና ምን የተለየ ትኩረት ተሰጥተዋል?
አቶ ዘመዴ አንዳርጌ: በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት መናኸሪያን በቴክኖሎጂ ማዘመን አስፈላጊ በመሆኑ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ተባብረን በክልሉ አየተገነቡ ያሉ ደረጃ አንድ የሚባሉ ሚዛን አማን፣ ቦንጋና ታርጫ መናሀሪያዎች ላይ የዲጅታል አገልግሎትን በመዘርጋት ከወረቀት ንኪኪ የፀዳ እንድሁም ቀልጣፋ ስምሪት እንዲሰፍን ለማድረግ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶችን እያጠናቀቅን ነው።
የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታየውን ጉድለት ለማረም መናሐሪያ ላይ የሚስተዋለውን አላስፈላጊ አሰራሮችና ግለሰቦችን መለየት ጠቃሚ በመሆኑ ባልተገባ ጥቅም ተጠምደው የስምሪት ስርዓቱን እያዛቡ ያሉ ግለሰቦች እንዲወጡ እየተደረገ ነው።
ረጅም ዓመታትን መናሐሪያ ላይ ቆይተው ለስምሪት ስርዓቱ መሰናክል የሆኑትን የማጥራት፣ የማስጠየቅና መልሰው የማደራጀት ስራዎች የጀመሩ ተቋማት አሉ። ለአብነትም እነ ቦንጋ፣ ቴፒ፣ ታርጫና ሚዛን አማን መናኸሪያዎች ይኸን ሪፎርም ከወድሁ ጀምረዋል።
ከዝህ ባሻገር የቁጥጥር ስራውን ለመስራት የትራፊክ ፖሊስና የመንገድ ደህንነት ዘርፍ ሰዎች በጋራ በተመረጡ ቦታዎች ላይ መቆም ሲገባቸው በተናጠል የሚቆሙት ላይም እርምት እርምጃ እየተወሰደ ነው፤ ተጠናክረውም ይቀጥላል።
መ/ኮ: ከትራፊክ ግጭት(አደጋዎችን) ለመቀነስ እየሰራችሁ ያለው ተግባራት ካሉ ቢጠቅሱልን
አቶ ዘመዴ አንዳርጌ: የትራፊክ ደህንነትን አደጋ ላይ ከሚጥሉት ነጥቦች አንዱና ትልቁ የአሽከርካሪዎች ብቃትና ስነምግባር ክፍተት ነው። ችግሩን ለማቅለል አሁን የተጀመረው ግምገማና ውይይት መድረኮች ከተጠናቀቁ በኃላ በከልል ደረጃ ለአሽከርካሪዎች የተሐድሶ ስልጠና ይሰጣቸዋል።
ከዚህ ጋር በተያዩያዘ የፌደራል ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚንስትር በቅርቡ በአዲስ አበባባ ከተማ ተግባራዊ ያደረገው የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ፈተና (COC) ወደ ክልሎች ወርደው ተግባራዊ ይሆናል። እነዚህ ሁሉ ሪፎርሞች ተግባራዊ ሲሆኑ በሰውና ንብረት ላይ የሚደርሰው ውድመቶች እንደሚቀንሱ እምነት አለን።
ሌላኛው የአደጋዎች መንስኤ የተሽከርካሪዎች ደህንነት የሚፈተሽበት የቴክኒክ ማዕክል በክልሉ ባለመኖሩ ተገልጋዮችን ከማጉላላት አልፎ አሰራሩንም ይፈትናል። ችግሩን ለመቅረፍም ባለሀብቶችን አወያይተን በሚዛንና ቦንጋ ከተሞች ተተክለው አገልግሎት እንዲሰጡ ፕሮፖዛል ቀርበው ቅድመ ዝግጅት ስራ እየተጠናቀቀ ነው።
ለአገልግሎት ብቁ ያልሆኑ ተሽከርካሪዎች ስምሪት ላይ መሆናቸው ለትራፊክ አደጋ ከፍተኛ ድርሻ ስላለው በጥንቃቄ ተፈትሸውና ተመርምረው ችግር ያለባቸው ከመስመር እንዲወጡ ይደረጋል።
ከዚህ በተጨማሪ ከትራፊክ ግጭት መንስኤዎችን ለመቀነስ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር እንዳይኖር ድንገተኛ ተቆጣጣሪ ቡድኖች ይንቀሳቀሳሉ። ይኸንን አሠራር የሚያግዝ የፍጥነት መቆጣጠሪያ ራዳር ቴክኖሎጂዎችን በተመረጡ ቦታዎች በማኖር የመከታተል ስራ ለመስራት ዝግጅቶች ተከናውኗል።
የባለ ሁለት እግር ሞተር አሽከርካሪዎች ራሳቸውን መከላከል የሚያስችለውን ሄልመት እንዲጠቀሙ የሚያስችል መመሪያ በክልላችን በጥሩ ሁኔታ እየተተገበረ ቢሆንም ከዝህ በተሻለ ደረጃ ለማስጠቀም የግንዛቤ እና ቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
መ/ኮ: በመንገድ ላይ ለሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች የመንገድ ድህንትና ሌሎች አካላት የራሳቸው ድርሻ ስላላቸው ምን የተለየ ትኩረት እየተሰጠ ነው?
አቶ ዘመዴ አንዳርጌ: በክልሉ በተደጋጋሚ የትራፊክ ግጭቶች በሚከሰትባቸው መንገዶች ላይ የተቀናጀ ጥናት በማካኸድ ማስተካከያዎች ለማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ነው። በእነዚያ አካባቢዎች ቅድመ ጥንቃቄ ሊሰጡ የሚችሉ ምልክቶች እንዲደረጉ እንድሁም ቀድመው የነበሩት እንዲታደሱ ይደረጋል።
የአሽከርካሪዎች ብቃት አሰጣጥ ሂደት አስተማማኝ እንዲሆን የትምህርትና ጤና ተቋማት ባለሙያዎች መረጃ ሲሰጡን የሰው ልጅ ህይወትን የሚወስን መረጃ በመሆኑ በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን።
የጤና ተቋማት ከእነዚህ መረጃዎች በተጨማሪ አንዳንድ የትራፊክ ግጭቶች በሚከሰቱበት ወቅት ድህረ አደጋዎችን በሚያስተናግዱበት ወቅት በመንግስት የተያዘ የመድህን በጀት እስኪደርሳቸው ድረስ የተለመደውን የሰው ህይወት የማዳን ስራቸውን በተሻለ ቅልጥፍና የሚሰሩበት አሰራሮችን ማሻሻል ያስፈልጋል።
ትምርት ቤቶችም በተማሪዎች ላይ የትራፊክ አደጋ አስከፊነትና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለውን ውድመት ማስገንዘብ፣ ቅድመ መከላከል መንገዶችን ለተማሪዎች ግንዛቤ መስጠት፣ ክበባትን ማቋቋምና የተማሪ ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን ማብቃት እና በአንዳንድ ትምህርት ዓይነቶች ላይ የይዘት አካል ሆኖ እንዲቀረጽ አትኩሮ መስራት ለውጤታማነቱ የላቀ ሚና ይጫወታሉ።
መ/ኮ: ከታሪፍ ውጭ በሚደረግ ክፊያዎችን ለማስቆም እተሰራ ያለው ስራ አበረታች ቢሆንም ከሁለቱም ወገን የሚነሳውን ቅሬታ ለመቀነስ ምን ታስበዋል?
አቶ ዘመዴ አንዳርጌ: ከታሪፍ ጋር ተያይዘው ከባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች የሚነሳውን ቅሬታ ለመፍታት የመንገድ ደረጃዎችን፣ የነዳጅ ዋጋን እና መለዋወጫ እቃዎችን ከግምት ያስገባ ወጥ የሆነ ታሪፍ ተመን በሀገር ደረጃ ወርደው ለትግበራ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
ነገር ግን ምንም ቢደረግ የለመድነውን ህገ ወጥነት ማቆም አንፈልግም የሚሉትን ለማስቆም ከባለድርሻ ተቋማትና ተሳፋሪዎች ጋር ሆነን እናርማቸዋለን። ይህ እውን የሚሆነው ደግሞ ህብረተሰቡ ራሱ ህገ ወጥነትን ከመተባበር ሲቆጠብ ብቻ ነው።
ፍትሐዊ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለመዘርጋት የእያንዳንዱ ዜጋ ተሳትፎ እጅጉን አስፈላጊ ስለሆነ ከመናኸሪያ እስከ መንገድ የተናበበ እና በቴክኖሎጂ የዘመነ አገልግሎት ለመዘርጋት የክልሉ መንግስት በአጽንኦት እየተንቀሳቀሰ ነው።
መ/ኮ: ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለዎት
አቶ ዘመዴ አንዳርጌ: አመሰግናለሁ፣ ቢሯችን በየደረጃ ያሉ ተቋማትን በማስተባበር የበኩሉን የሚወጣ ቢሆንም ህብረተሰቡ ካልተባበረን ምንም ለውጥ ሊመጣ አይችልምና ትርፍ ከመጫን እና ከፍጥነት በላይ በማሽከርከር የሚመጣውን አደጋ እንድሁም ከታሪፍ በላይ ክፊያ የሚመጣውን የኢኮሚ ጫና ለመቀነስ አስፈላጊውን ጥቆማ በመስጠት የተጀመረውን የቁጥጥር ስራ ወደ ባህል እንዲያሳድጉ ጥሪ አቀርባለሁ።
በመጨረሻም የግንዛቤውን ስራ እንደየ አውዳቸው የትምህርት ተቋማት፣ የሀይማኖት ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከወትሮ በተሻለ መልኩ እንዲያጠናክሩ እንድሁም በክልላችን ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የሚዲያ ተቋማት ይኸንን ተግባር በአጽንኦት እንዲያስተባብሩ አደራ እላለሁ።
መ/ኮ: በዚህ ጉዳይ ላይ ለሰጡን ምላሽና ማብራሪያ በተቋማችን ስም አመሰግናለሁ!
አቶ ዘመዴ አንዳርጌ: እኔም አመሰግናለሁ!
በአሻግሬ ገ/ወልድ
