የዲጂታል ጤና አገልግሎቶችን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ጤንነቴ የሞባይል መተግበሪያ የኢፌድሪ ፕሬዝደንት ታዬ አስቃስላሴ በተገኙበት ይፋ ተደረገ

Spread the love

ጤና ሚኒስቴር “ጤንነቴ የሞባይል መተግበሪያን” በአዲስ አበባ የሳይንስ ሙዚየም በመካሄድ ላይ በሚገኘው የዲጂታል ጤና ኮንፈረንስ እና ኤግዚቢሽን የመክፈቻ መርሃግብር ላይ ይፋ አድርጓል።

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የኢትዮጲያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት፣ ታዬ አስቃስላሴ ጤንነቴ የሞባይል መተግበሪያ ይፋ መሆኑን በመግለጽ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተዘጋጀዉን የዲጂታል ጤና ኮንፈረንስ እና ኤግዚቢሽን በይፋ ከፍተዋል።

መንግስት የጤናው ዘርፍን ለማሳደግ እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎችን የኤፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀስላሴ ያብራሩ ሲሆን፤ ጤና ሚኒስቴር የጤና ስርዓቱን ለማዘመን እያደረገ የሚገኘውን ጥረት አድንቀዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸዉ ጅምሩ የኢትዮጲያን የጤና ስርዓት በቴክኖሎጂ ዘመናዊ ለማድረግ እና ለህብረተሰቡ ትክክለኛ የጤና መረጃን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ እርምጃ መሆኑን በመግለጽ የመድኃኒት አቅርቦትን ማሻሻል እና በጤና ዲጂታይዜሽን እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን አብራርተዋል።

ዲጂታል ጤና ሁለንተናዊ የጤና ሽፋንን ለማድረስ እና ጠንካራ የጤና ስርዓትን ለመገንባት ቁልፍ መሆኑን ዶ/ር መቅደስ አፅንዖት ሰጥተዋል።

አዲሱ የጤንነቴ የሞባይል መተግበሪያ ዜጎች ስለ መድሃኒት አቅርቦት፣ የጤና አገልግሎቶች እና የጤና መረጃ ን በቀጥታ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ተገልጋዮች እንክብካቤን በፍጥነት እንዲያገኙ እና አላስፈላጊ ጉዞን እንዲቀንሱ ይረዳል።

አገልግሎቱ በአዲስ አበባ በይፋ መጀመሩ የተገለጸ ሲሆን በቀጣይም በመላ ኢትዮጵያ አከባቢ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል።

አፕሊኬሽኑ የዲጂታል ጤና ስርዓት ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ፣ ለታካሚዎች የታዘዙ መድሃኒቶች የት እንደሚገኙ በቀላኡ መረጃ የሚሰጥበት ሆነዉ ለበጎ የተሰኘ ዘመናዊ የአምቡላንስ መላኪያ ስርዓት እና 952 ብሔራዊ ነጻ የጤና ጥሪ ማዕከልን ያካተተ ነዉ። በዚህም የአደጋ ጊዜ ምላሽን ፈጣን ለማድረግ እና የጤና መረጃ ለሁሉም ሰው በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

በፕሮግራሙ ላይ የክልል ፕረዝደንቶች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲበን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ከፍተኛ ስራ ሀላፊዎች እንዲሁም የአጋር ድርጅቶችና የግሉ ዘርፍ ተወካዮች የተገኙ ሲሆን ለሁለት ቀናት የሚቆየው ኮንፈረንስ “ሕይወትን ለማዳን ዲጂታል ጤናን፡ የመድኃኒት መረጃ አገልግሎት ተደራሽነትን ማሳደግ” በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ሲሆን፤ በአይነቱ ልዩ የሆነ የዲጂታል ጤና ኤግዚቢሽንም ለሚቀጥሉት 2 ቀናት ክፍት እንደሚሆን መገለፁን የሚኒስቴር መሥሪያቤቱ መረጃ ያመለክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *