ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ሕብረት የተፈራረሙትን ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማጠናከር ይገባል- ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

Spread the love

ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ሕብረት የተፈራረሙትን ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በአውሮፓ ሕብረት የውጭ ግንኙነት አገልግሎት የኢኮኖሚ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሐፊ ሳይመን ሞርዱ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እና አውሮፓ ሕብረት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በየጊዜው ምክክር ማድረጉ ጠቃሚ መሆኑን በውይይቱ ላይ አንስተዋል።

ጌዲዮን (ዶ/ር) ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ሕብረት እ.ኤ.አ 2016 የተፈራረሙትን ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት መልሶ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

አውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚ ልማት ትብብር፣ በኢንቨስትመንት፣ በቀጣናዊ ሰላም እና ጸጥታ ዙሪያ የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ በማንሳት ለምክትል ዋና ፀሐፊው በቀጣናዊ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ገለጻ አድርገውላቸዋል።

ምክትል ዋና ጸሐፊ ሳይመን ሞርዱ የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ ሕብረት ጋር ያለውን ግንኙነት ጨምሮ የበለጠ ማጠናከር እንደሚፈልግ ገልጸዋል።

የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚ የልማት ትብብር፣ በሥራ ፈጠራ፣ ኢንቨስትመንት ጋር የሚያደርገው ትብብር ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባለፈ ቀጣናዊ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል።

የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር ላለው ግንኙነት የተለየ ትኩረት እንደሚሰጠውም ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ እና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኢመስበርገር መገኘታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *