




የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ በተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ የምክር ቤቱን ሁለት ቀናት ውሎ አስመልክቶ ማጠቃለያ ሀሳብ ሰጥተዋል ፡፡
አፈ ጉባኤ ወንድሙ ኩርታ በሰጡት ማጠቃለያ ሀሳብ በክልሉ በአስፈጻሚ ተቋማት የተሻሉ አፈጻጸሞች መኖራቸውን አመላክተዋል ፡፡
ዋና አፈ ጉባዔዉ ከአስፈጻሚ ተቋማት አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ፣ጤና ቢሮ፣ገቢዎችና ሴቶችህ ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ተቀናጅተዉ እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል።
በጤና ስራዎች በተለይም የወባ በሽታን ለመከላከል የተሰሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል
በትምህርት ስራዎች በተለይም የተማሪዎች ምገባ ስርኣት መጀመር፣የትምህርት ግብኣት የማሟላት ስራዎች የሚበረታቱ ቢሆንም በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ መስራት ይገባል ፡፡
የጤና መድህን ስርዓትን ከማጠናከር አኳያ ምክር ቤት አባላት ግንባር ቀደም ሆነው ለተግባራዊነቱ ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባልም ብለዋል ፡፡
በጤና ተቋማት የሚሰጠውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ለጤና ተቋማት የሚወርዱ በጀቶች በተገቢው ስለመመደቡ ምክር ቤት አባላት በየምርጫ ክልላቸው ሊፈትሹና ሊያርሟቸው እነደሚገባም አሳስበዋል ፡፡
ክልላዊ ገቢ የመሰብሰብ አቅማችንን በመጠቀም ክልላዊ የመሰረተ ልማት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል ፡፡
የደረጃ ሽግግር የሚያደርጉ ግብር ከፋይ ነጋዴዎችን በተገቢው በመለየት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል፡
በአስፈጻሚ ተቋማት ተከናውነው የቀረቡ ሪፖርቶች በትክክል የተሰሩ ስለ መሆናቸው በተገቢው ማረጋገጥ ያስፈልጋል ያሉት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ ለምክር ቤት አባላት ግርታን በሚፈጥር መልኩ መቅረብ የለባቸውም ሲሉ አሳስበዋል ፡፡
በወረዳና ከተማ አስተዳደሮች ያሉ የህብረት ስራ ማህበራት ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል የማጠናከርና የመደገፍ ስራዎች ሊጠናከሩ ይገባልም ብለዋል አፈ ጉባኤ ወንድሙ ፡፡
በስራ ዕድል ፈጠራም የዜጎች ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መንገድ በተጨባጭ ትኩረት በመስጠት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል ፡፡
በቡናና ሻይ ልማት ስራዎች የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር ክልላዊ ሽፋን ማሳደግና ጥራት ያለውን ምርት ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ የተሸለ ገቢ ለማግኘት ትኩረት በመስጠት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።
ከእንስሳት ሀብት አኳያ በተለይም በዶሮ እርባታ ስራዎች ያለውን ስራ የበለጠ ውጤታማ በማድረግ በከተሞች የእንቁላል ምርት አቅርቦትን ማሻሻል ይገባል ብለዋል ፡፡
ከነዳጅ ጋር በተያያዘም ህገ ወጥነትን የሚያባብሱ ግለሰቦችን ከመዋቅር ውስጥ በመፈተሸ ተጠያቂ ማድረግ ስራ ሊሰራ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል ፡፡
በወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች አካባቢ የሚገኙ መንገዶችን ሁሉም ድርሻውን በመውሰድ የጥገና ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባቸውም አብራርተዋል ፡፡
የተበላሹ አሰራሮች እንዳይከሰቱ አስቀድሞ ለመከላከል የኦዲት ስራዎችን በየደረጃው አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባልም ብለዋል ፡፡
በቀጣይም የተሻለ አፈጻጸም በሁሉም ተቋማት ትኩረት በመስጠት ማከናወን እነደሚገባ በማሳሰብ የምክርቤቱ ጉባኤ ተጠናቋል ፡፡
በታጠቅ አበበ
