የክልሉን ህዝብ የልማት ፍላጎት ለማሟላት መንግስት ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው ።ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ።

Spread the love

የክልሉን ህዝብ የልማት ፍላጎት ለማሟላት መንግስት ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው ሲሉ ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናግረዋል ።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቤንች ሸኮ ዞን በጊዲ ቤንች ወረዳ የተገነባ አነስተኛ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ተደርጓል ።

በዚሁ የምረቃ ፕሮግራም መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በክልሉ 29 ሺህ ሄክታር ማልማት የሚችል የመስኖ ልማት ጥናትና ዲዛይን በ194 ሚሊዮን ብር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዘንድሮ በጀት ዓመትም 8 የተለያዩ አነስተኛ የመስኖ አውታሮች ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል ።

ዛሬ የተመረቀው የፔቱ አነስተኛ የመስኖ ልማት አውታር ህብረተሰቡ በመጠበቅና በመንከባከብ በኃላፊነት ጥቅም ላይ መዋል አለበትም ብለዋል።

አርሶአደሮች በማህበር ሆነው ማልማት እንዳለባቸውና ምርታቸውንም በማህበር ተደራጅተው ወደ ገበያ ማቅረብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የፔቱ አነስተኛ መስኖ ልማት ተሰርቶ እስኪጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ ተባባሪ አካላት በክልሉ መንግስት ስም አመስግነዋል ።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው የፔቱ አነስተኛ መስኖ ልማት በኤጂፒ 2 ፕሮግራም የተጀመረና ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት ተናግረዋል ።

በክልሉ የፔቱን ጨምሮ መራጫና ኡፊያ አነስተኛ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በዳውሮና ካፋ ዞኖች በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል ።

የፔቱ አነስተኛ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት አገልግሎት ሲሰጥ ከ1215 በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

የቤንች ሸኮ አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን በበኩላቸውም የፔቱ አነስተኛ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት አርሶአደሮችን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ በዓመት 3 ጊዜ በማረስ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

የፔቱ መስኖ ልማት አገልግሎት ሲሰጥ ህዝቡን ከተረጂነት በማላቀቅ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።

በፕሮግራሙ ለፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረኩት አካላት የምስጋናና የዕዉቅና ምስልር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *