



የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበትና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበት ሁኔታ ለመወሰን የወጣውን የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ አጸደቀ።
ምክር ቤቱ ባካሄደው 34ኛ መደበኛ ስብሰባው የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበት እና የልማት ተነሺዎች የሚቋቋሙበት ረቂቅ አዋጅን አፅድቋል።
ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፊ ውይይት ያካሄደ ሲሆን በአብላጫ ድምጽ አድቋል።
የከተማ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሸዊት ሻንካ በሰጡት ማብራሪያ አዋጁ ካሳን ለመተመን፣ ለመክፈልና ተነሺዎችን መልሶ ለማቋቋም ስልጣንና ኃላፊነት ያለባቸውን አካላት በግልጽ ለይቶ ለመወሰን የሚያስችል ስርአት ዘርግቷል።
ፕሮጀክቶች በጥራት እና ግዜ ቆጣቢ በሆነ መልኩ እየተከናወኑ ለአገርና ለህዝብ ጥቅም ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍ እንዲል የሚያደርግ ድንጋጌ ማካተቱንም ገልጸዋል።
ክልሎች ካሳ ክፍያውን የመፈጸም ሙሉ ሃላፊነት እንዳላቸውም በአዋጁ ላይ መቀመጡን አብራርተዋል።
ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የባንክ ስራ ረቂቅ አዋጅ ላይም የተወያየ ሲሆን ለዝርዝር እይታ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
