የህዝቦች የወል ታሪክ ለጠንካራ የሀገር መንግስት ግንባታ ያለውን ሚና በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም ገለጹ

Spread the love

የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ጋር በመተባበር “ታሪክ ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት ግንባታ” በሚል መርህ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም፤ የሀገር ግንባታ ሥራ ከታሪክ አስተምህሮ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ትውልዱ የትናንቱን ታሪክ ተረድቶ ከዛሬው ጋር እያቆራኘ እንዲሄድና እሴቱን እንዲጠብቅ የታሪክ ባለሙያዎች ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

በተለይ የህዝቦች የወል ታሪክ ለጠንካራ የሀገር መንግስት ግንባታ ያለውን ሚና በአግባቡ መጠቀም ይገባል ነው ያሉት፡፡

ታሪክ በኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ውስጥ ትውልድን በአግባቡ እየቀረጸ ለመሄድ የማይተካ ሚና እንደሚጫወት በመጠቆም፡፡

የኢትዮጵያ ታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ኤመሪተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፤ ማኅበሩ እንደገና ከተመሠረተ የካቲት 23 ቀን 2013 ወዲህ በርካታ ስኬታማ ሥራዎችን መሥራቱን ተናግረዋል።

ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ተቋርጦ የነበረውን የጋራ የታሪክ ኮርስ እንደገና ማስጀመር መቻሉን ተናግረዋል፡፡

” ትስስርና መስተጋበር በኢትዮጵያ ታሪክ ” በሚል ርዕስ ሦስት ተከታታይ ዐውድ ጥናቶችን በማካሄድ የጥናታዊ ጽሁፎቹን ማሳታም መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

ታሪክ ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ የበኩሉን እንዲያበረክትም እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ታሪክ የችግር ሳይሆን ሁሌም የመፍትሔው አካል ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

በመድረኩ የብሔረሰባዊና አገራዊ ታሪክ ተዛምዶ በሚል ርዕስ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶክተር መሐመድ ሐሰን በኢትዮጵያ ከጦር ሜዳ ገድል ጎን ለጎን በተለያዩ የህይወት መስኮችና በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ሊነገሩ የሚገቡ ታሪኮች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም ትውልዱ ሊማርባቸው ከሚገቡ ጀግንነቶች መካከል በዲፕሎማሲ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በስፖርት እንዲሁም በአከባቢ ጥበቃ መስኮች የፈጸሟቸው ታሪኮች ሊነገሩ እና ለትውልድ ሊተላለፉ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንዲህ ያሉ መድረኮች ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንደ ግብዓት የሚገለግሉ ናቸው ብለዋል፡፡

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሌለኛው የመድረኩ ተሳታፊ መሐመድ አብዱላሂ የወል ታሪኮችን በማጉላት ለሀገር መንግስት ግንባታ መዋል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በተካሄደው የምክክር መድረክ ሚኒስትሮች፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የታሪክ ምሁራን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *