19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በቦንጋ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበረ

Spread the love

“ሀገራዊ መግባባት ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቦንጋ በከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ የካፋ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ ግርማ ደፋር፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዝሃ ማንነት ያሉባቸው ሀገር በመሆኗ ይህንን የብዝሃ ማንነት ማስተናገድ የሚያስችል የበለፀገ ዴሞክራሲና እውነተኛ ፌዴራላዊ ስርዓት መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ለዚህም በብሔር ማንነትና በሀገራዊ ማንነት መሀል ሚዛኑን የጠበቀ የፖለቲካ ሥርዓት በመገንባት አካታችና ህብረ-ብሔራዊ ጠንካራ ሀገር መገንባት የለውጡ አንዱና ዋናኛ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል በየዓመቱ መከበር በአንድ ሀገር ውስጥ እየኖሩ የማይታወቁ የነበሩ ማንነቶችና ቋንቋዎች እንዲሁም ባህሎች ሰፊ እድል ከመፍጠሩም ባሻገር የአብሮነት ስሜት በተሸለ መልኩ እንዲያጎለብቱ አስችሏል ብለዋል፡፡

19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል “ሀገራዊ መግባባት ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል የተመረጠበት ምክንያት በሀገራችን ስር የሰደዱ አንዳንድ አለማግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ለማስቻል መሆኑን የተከበሩ አቶ ግርማ ገልፀዋል፡፡

የካፋ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ለመጠናከር አንዳንድ የሚታዩ አለማግባባቶችን በመወያየት እና በመመካከር መፍታት ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ እንዳሻው ከበደ አክለውም አንድነትን፣ ሠላምንና ኢኮኖሚን በማጠንከር የዞናችን፣ የክልላችን ብሎም የሀገራችንን አንድነት መጠበቅ ከሁላችንም የሚጠበቅ በመሆኑ ለዚህም ሁላችንም ተግተን መስራት አለብን ብለዋል፡፡

በመድረኩ “ህብረ-ብሔራዊ ፌዴራል ሥራዓት በኢትዮጽያ ተግዳሮቶች እና የመፍትሄ ሀሳቦች” በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀ የሠነድ የቀረበ ሲሆን አጠቃላይ አመራሮችና ሰራተኞች በተገኙበት ውይይት ተደርጓል።

በበዓል አከባበር ላይ የብሔር ብሔረሰቦችን ባህላዊ እሴቶችን የሚያንፀባርቁ ትዕይንቶች የቀረበና የተማሪዎች ጥያቄና መልስ ውድድር ተካሂዶ ሽልማት በማበርከት መድረኩ ተጠናቋል፡፡

በበዓሉ ላይ የክልሉ ዋና ኦዲተር አቶ አስራት አበበ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ አቶ ንጉሴ ወ/ጎርጊስን ጨምሮ የቦንጋ ማዕከል የክልል ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች፣ የካፋ ዞንና የቦንጋ ከተማ አስተዳደር አመራሮችና ሠራተኞች እንዲሁም የፀጥታ መዋቅር አመራሮችና አባላት ተሳትፈዋል፡፡

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *